ኢራን ከሩሲያ ተዋጊ ጄቶችን ለመግዛት መስማማቷን አስታወቀች
ቴህራን በርካታ ያረጁ ተዋጊ አውሮፕላኖቿን በአዲስ ለመተካት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ንግግር እያደረገች መሆኑንም ነው የገለጸችው
ሩሲያ በበኩሏ ከኢራን ጋር ስለተደረሰው የተዋጊ አውሮፕላን ሽያጭ ማረጋገጫ አልሰጠችም
በመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀቦች ምክንያት ክፉኛ የተጎዳው የኢራን አየር ሃይል ዘመናዊ የጦር ጄቶችን ሊታጠቅ መሆኑ ተገልጿል።
ቴህራን ከሩሲያ “ሱክሆይ 35” ወይም ሱ - 35 የተሰኙትን የጦር ጄቶች ለመግዛት ከስምምነት ላይ መድረሷን የኢራን ብሄራዊ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በመንግስታቱ ድርጅት የኢራን ልዩ መልዕክተኛን ዋቢ ያደረገው ዘገባ ምን ያህል የጦር አውሮፕፕላኖች እንደሚገዙ አልጠቀሰም።
ሩሲያም እስካሁን ስለሽያጩ ማረጋገጫ ባትሰጥም የኢራን አውሮፕላን አብራሪዎች ይህንኑ ተዋጊ ጄት ማብረር የሚያስችል ስልጠና ሲወስዱ መቆየታቸን ፍራንስ 24 አስታውሷል።
ኢራን ከ1980 ጀምሮ ከኢራቅ ጋር በነበራት ጦርነት ምክንያት የአየር ሃይሏ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሏት የሶቪየት ዘመን ሚግ፣ የአሜሪካ ኤፍ 4 እና ኤፍ 5 እና የተወሰኑ የቻይና ኤፍ 7 ተዋጊ አውሮፕላኖች ናቸው።
በሀገሪቱ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች አዳዲስ የጦር አውሮፕላኖችን መግዛት ሳያስችሏት በመቅረታቸው በ2018 “ኮውሳር” የተሰኘ የጦር አውሮፕላን በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሯ ይታወሳል።
አሁን ላይ ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት የመሰረተችው ቴህራን ፥ ከሱ-35 የጦር ጄቶች ባሻገር ለተለያዩ ወታደራዊ ተልዕኮዎች የሚውሉ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከተለያዩ ሀገራት ጋር እየተናገረች ነው ተብሏል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው አመት በቴህራን ከኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ጋር ሲመክሩ የምዕራባውያንን ጫና በጋራ ስለመመከት መምክራቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ቴህራን ድሮኖችን ለሞስኮ በመሸጥ ይህንኑ ትብብር ማሳየቷን የሚያነሳው ዘገባው፥ የሱ - 35 የጦር ጄቶች ስምምነቱም የሀገራቱን ወዳጅነት እየጠበቀ መሄድ ያሳያል ብሏል።
ኢራን የአየር ሃይሏን ለማጠናከር ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከየትኞቹ ሀገራት ጋር እየተነጋገረች መሆኑ አልተገለጸም።
አሜሪካ በ2019 ከኢራን የኒዩክሌር ስምምነት በመውጣት በተለያዩ ዘርፎች ዳግም ማዕቀቦችን መጣል መጀመሯ ኢራን ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ያላትን ትብብር እንድታጠናክር አድርጓል።