ኢራን በምድር ውስጥ የገነባችውን የጦር አውሮፕላኖች ማረፊያ አስተዋወቀች
ቴህራን “ኤግል 44” የተሰኘው የአየር ሃይል ማዘዣ ጣቢያ ከእስራኤል ለሚቃጡ ጥቃቶች ምላሽ መስጫ መሆኑን ገልጻለች
ኢራን በባላንጣዎቿ የሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን ሽሽት የምድር ውስጥ ወታደራዊ ጣቢያዎችን በመገንባት ላይ ትገኛለች
ኢራን የመጀመሪያውን የምድር ውስጥ የአየር ሃይል ማዘዣ ጣቢያዋን ትናንት አስተዋውቃለች።
“ኤግል 44” የሚል መጠሪያ የተሰጠው የጦር አውሮፕላኖች ማረፊያ ጣቢያን የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መርቀው ከፍተውታል።
በጣቢያው የጦር ጄቶች ሲንቀሳቀሱና ለተልዕኮ ሲሰማሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልንም የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል (ኢርና) አስመልክቷል።
በኢራን ወታደራዊ ፋብሪካ ላይ እስራኤል ጥቃት ፈጽማለች - የአሜሪካ ባለስልጣናት
የምድር ውስጥ የአየር ሃይል ማዘዣ ጣቢያው “እስራኤልን ጨምሮ ከማንኛውም የኢራን ጠላት ለሚቃጣ ጥቃት ምላሽ የሚሰጡ አውሮፕላኖች ያርፉበታል” ብለዋል የኢራን ጦር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሞሃመድ ባግሄሪ።
“ኤግል 44” ረጅም ርቀት የሚምዘገዘጉ ክሩዝ ሚሳይሎችን የታጠቁ የጦር ጄቶች የሚከማቹበት እንደሚሆንም ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቴህራን ትልቅ ስፍራ የሰጠችውን ወታደራዊ ጣቢያ ከአደጋ ለመጠበቅ ስትል የተገነባበትን አካባቢ ይፋ አላደረገችም።
ይሁን እንጂ የምድር ውስጥ ጣቢያው የአሜሪካም ሆነ የእስራኤልን የቦምብ ጥቃቶች እንዲቋቋም ተደርጎ ስለመገንባቱ ነው የተነገረው።
ቴህራን ወታደራዊ ጣቢያውን እና በውስጡ የሚገኙ የጦር ጄቶችን ለእይታ ያበቃችው ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ካደረጉ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው።
ከዚህ ልምምድ አስቀድሞም ኢራን ወታደራዊ ዝግጁነቷን የሚያመላክት ሰፊ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ይታወሳል።
የትናንቱ የምድር ውስጥ የአየር ሃይል ማዘዣ ጣቢያ ትውውቅም ለባላንጣዎቿ መልዕክት የሰደደችበት ነው ብሏል የኢራን ብሄራዊ ዜና አገልግሎት (ኢርና)።
በጣቢያው ውስጥ የሚገኙ የጦር ጄቶች ብዛት ባይገለጽም “በቀጠናው ያለንን የአየር ሃይል የበላይነት ያሳያል”ም ነው ያለው ዘገባው።
ባለፈው ሳምንት በኢስፋን በሚገኘው የኢራን ወታደራዊ ፋብሪካ የተቃጣው የድሮን ጥቃት በሌሎች የኒዩክሌር ጣቢያዎችም ላይ እንዳይፈጸም ቴህራን ስጋት አላት።
ኢራን ሻሄድ 136 የተሰኙ ድሮኖችን የምታመርትበት ፋብሪካን በድሮን ለመምታት የሞከረችው እስራኤል እንደሆነች ታምናለች።
በትናንትናው እለትም አዲሱን የምድር ውስጥ የአየር ሃይል በማስተዋወቅ ቴል አቪቭን “በእሳት አትጫዎቺ” የሚል መልዕክት እንደላከችላት ይታመናል።
ሀገሪቱ ሚሳኤልና ድሮኖችን በምድር ውስጥ የምትደብቅባቸውን መሰል የምድር ውስጥ ጣቢያዎች በስፋት በመገንባት ላይ እንደምትገኝ ይነገራል።
ባለፈው አመትም በዛግሮስ ተራራ አካባቢ የገነባችውንና ከ100 በላይ ድሮኖችን መያዝ የሚችለውን የምድር ውስጥ ወታደራዊ ጣቢያዋን ማስተዋወቋ የሚታወስ ነው።
በቀደመው የስልጣን ዘመናቸው በኢራን እና ሶሪያ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ያዘዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዳግም ወደ መንበራቸው መመለሳቸውም የሀገራቱን ሰጣ ገባ ይበልጥ እንዳይጨምረው ያሰጋል።