አረብ ኤምሬትስ ሃማስ እና እስራኤል ግጭት እንዲያቆሙ ጠየቀች
ሁለቱም ወገኖች ንጹሃንን አደጋ ላይ ከሚጥሉ እርምጃዎች እንዲቆጠቡም ነው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ያሳሰበው
ኤምሬትስ ወቅታዊው ግጭት ቀጠናዊ መልክ እንዳይዝ በፍጥነት በንግግር መፍትሄ ያሻዋል ብላለች
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሃማስ እና እስራኤል ውጥረት እንዲረግብ ጠየቀች።
ተፋላሚዎቹ ወገኖች ለንጹሃን ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ግጭት ሊያቆሙ እንደሚገባ ነው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሳሰበው።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፥ “ሃማስ ንጹሃን ወደሚገኙባቸው የእስራኤል ከተሞችና መንደሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኰቶችን መተኮሱ አደገኛ ነው፤ ውጥረቱንም ያንረዋል” ብሏል።
ኤምሬትስ “እስራኤላውያን ንጹሃን ዜጎች ታፍነው ተወስደው ምርኮኛ እንዲሆኑ በመደረጉም አዝናለች” ነው ያለው መግለጫው።
ሁለቱም ወገኖች (ሃማስ እና የእስራኤል ጦር) በአለማቀፉ የሰብአዊነት ህግ መሰረት የንጹሃንን ደህንነት ማስጠበቅ እንዳለባቸውና ንጹሃንን የጥቃት ኢላማ ከማድረግ እንዲታቀቡ አሳስቧል።
ኤምሬትስ በሰሞኑ ግጭት ህይወታቸው ላለፈ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን ቤተሰቦች ሀዘኗን በመግለጽ፥ ግጭቱ ቀጠናዊ መልክ ከመያዙ በፊት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች።
“የተለያዩ ሃይላት በግጭቱ መሳተፍ ጀምረው አድማሱን እያሰፋ እንዳይሄድ አለማቀፉ ማህበረሰብ በጋራ መስራት አለበት” ያለው የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፥
ወቅታዊው ግጭት በጦርነት ብዙ ዋጋ ለከፈለ ህዝብ መፍትሄ ለማበጀት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን እንደሚያውክ አብራርቷል።
ኤምሬትስ ከቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ አጋር ተቋማት እና ሀገራት ጋር በመሆን ውጥረቱ በፍጥነት እንዲረግብና እስራኤልና ፍልስጤም ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን ሰላምና ክብራቸው ተጠብቆ የሚኖሩበት የመጨረሻ ስምምነት (ፍልስጤም ነጻ ሀገር የምትሆንበት) እንዲደረስም ትሰራለች ነው ያለው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።