ኢራን በሁሉም መስመሮች በረራ አቋረጠች
የሀገሪቱ ሱቪል አቪየሽን ባለስልጣን በቀጣይ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ ከኢራን የሚነሱም ሆነ በኢራን የሚያርፉ በረራዎች ተቋርጠዋል ብሏል
እስራኤል ዛሬ ማለዳ በኢራን ላይ የአጻፋ እርምጃ መውሰዷን ተከትሎ በኢራን የአየር ክልል የሚደረግ በረራ ቆሟል
ኢራን መነሻ እና መዳረሻቸውን ወደ ሀገሪቱ ያደረጉ ሁሉንም በረራዎች እንዲቋረጡ ማድረጓን አስታወቀች።
የሀገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ቃል አቀባይ ጃፋር የዝርሉ “በቀጣይ እስክናሳውቅ ድረስ ሁሉም በረራዎች ተቋርጠዋል” ማለታቸውን የኢራኑ ብሄራዊ የዜና ወኪል ኢርና አስነብቧል።
ቴህራን በረራዎች እንዲቋረጡ ያደረገችው በእስራኤል ከተሰነዘረባት ጥቃት ከስአታት በኋላ ነው።
የበረራ መረጃዎችን የሚያጋራው ፍላይት ራዳር የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ የኢራን የአየር ክልል ከአውሮፕላኖች ነጻ መሆኑን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል።
የኢራን አየር ሃይል እስራኤል በቴህራን ኩዜስታን እና ኢማን ግዛቶች ሊፈጽመው የነበረውን ጥቃት ማክሸፍ መቻሉን ገልጿል።
በተወሰኑ አካባቢዎች መጠነኛ ጉዳት መድረሱን የጠቀሰው ታስሚን የዜና ወኪል በበኩሉ ቴህራን ለቴል አቪቭ ጥቃት አጻፋውን እንደምትመልስ መዛቷን ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳኔል ሃጋሪ በሰጡት መግለጫ “እስራኤል ግቧን አሳክታለች፤ እስራኤልን የሚተነኩሱ ከባድ ዋጋ ይከፍላሉ” ብለዋል።
ቴህራን ሌላ ዙር ጥቃት በእስራኤል ላይ ከፈጸመች ቴል አቪቭ ከበድ ያለ የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ መናገራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
“መልዕክታችን ግልጽ ነው፤ እስራኤል ላይ አደጋ የሚደቅንና ቀጠናውን ወደ ከፋ ውጥረት የሚከት አካል ከባድ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉም ተደምጠዋል።
እስራኤል የዛሬውን ጥቃት የፈጸመችው በጥቅምት ወር መጀመሪያ ኢራን 200 በሚጠጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ለፈጸመችባት አጻፋውን ለመመለስ ነው።
ቴህራን ግን ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት መጠነኛ ጉዳት ማድረሱን ከመግለጽ ውጭ እስራኤል ስኬታማ ነበር ስላለችው የአጻፋ ጥቃት ጉዳት ዝርዝር መረጃ አልሰጠችም።