ሀገራት ለሊባኖስ 1 ቢሊዮን ዶላር ሰብአዊና ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ
ፈረንሳይ ባዘጋጀችው ጉባኤ ከ70 ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች እና ተወካዮቻቸው ተሳትፈዋል
የሊባኖስ ጦር በተዋጊዎች ብዛትም ሆነ በትጥቅ ከሄዝቦላህ ያነሰ አቅም ያለው ነው
በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው የሊባኖስ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለቤሩት 1 ቢሊዮን ዶላር ሰብአዊ እና ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ተገብቷል።
የገንዘብ ድጋፉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያፈናቀለው እና ከ2500 በላይ ሰዎች የሞቱበት ፤ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል እየተደረገ የሚገኝው ጦርነት የኢኮኖሚ ቀውስ ያባባሰባትን ሀገር ለመርዳት የሚውል ነው ተብሏል፡፡
ከ70 በላይ ሀገራት እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል በተባለው የፓሪሱ ጉባኤ 800 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ዕርዳታ እና 200 ሚሊዮን ዶላር የፀጥታ ኃይሎችን ለማጠናከር የሚውል ድጋፍ መሰብሰቡን የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት ተናግረዋል፡፡
በጉባኤው ላይ አሜሪካ 300 ሚሊየን ዶላር ፣ ፈረንሳይ 100 ሚሊየን ዶላር ፣ ጀርመን 96 ሚሊየን ዩሮ ፣ ጣሊያን 10.8 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሊባኖስ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ 426 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጾ ነበር፡፡
ሆኖም በሊባኖስ መደበኛ ባልሆነ እና በጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ጥገኝነት ፣ ግልፅነት የጎደለው አሰራር እና ሙስና እርዳታ የማድረስ ሂደቱን ፈታኝ ሊያደርግ እንደሚችል ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው፡፡
የፓሪሱ ኮንፈረንስ የሊባኖስ የጸጥታ ኃይሎችን ለማጠናከር ዓለም አቀፍ ድጋፍን በማስተባበር ጦርነቱን ለማቆም በሚደረገው ጥረት በደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍል እንዲሰማሩ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
ይህ ለሊባኖስ ጦር የሚሰጠው ድጋፍ በጤና እንክብካቤ፣ በነዳጅ፣ አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች መርዳት ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተጨማሪም 6000 ተጨማሪ ወታደሮችን ለመመልመል እና 8000 ተጨማሪ ወታደሮችን በደቡብ ሊባኖስ ማሰማራትን ያጠቃልላል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግስት ምስርታ ላይ ያልተስማሙባት ሀገር ለሁለት አመታት ያለ ፕሬዝዳንት በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እየተመራች ትገኛለች፡፡
ሄዝቦላህ በሀገር ውስጥ የራሱን ሀገር መስርቶ የሚያስተዳድርበት ስርአት ማብቃት አለበት ያሉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑየል ማክሮን፥ የሊባኖስን ሉዓላዊነት ለመመለስ እና ተቋሞቿን ለማጠናከር ፓሪስ ድጋፍ ማድረግ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡
በአምስት ዓመታት የኢኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ የተመታው የሊባኖስ ጦር በእጁ ላይ በሚገኙት ያረጁ ጦር መሳሪያዎች እና ያለምንም የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂ የእስራኤልን ወረራ ለመከላከል ወይም ከሂዝቦላህ ጋር ለመፋለም የሚያስችል አቅም እንዳይኖረው ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሊባኖስ ጦር ወደ 80 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ያሉት ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ ታጣቂዎች እንዳሉት የሚነገርለት ሄዝቦላህ በበኩሉ በኢራን በሚደረግለት ድጋፍ በትጥቅ እና ተዋጊዎች ከሀገሪቱ ጦር የላቀ ቁመና እንዳለው አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል፡፡