ከ100 በላይ የሊባኖስ የጤና ተቋማት በጦርነቱ ምክንያት ተዘግተዋል - ዶክተር ቴድሮስ
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ በእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት ሲቪሎች፣ የጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል
ድርጅቱ በጦርነቱ ለተጎዱ ከ12 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ለመድረስ በአፋጣኝ ተኩስ አቁም እንዲደረስ ጠይቋል
እስራኤል በሊባኖስ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት ከ100 በላይ የጤና ተቋማት መዘጋታቸውን የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ።
በጦርነቱ ምክንያት ለመዘጋት የተገደዱት የጤና ተቋማት ከሊባኖስ አጠቃላይ የህክምና መስጫዎች ውስጥ ሲሶውን እንደሚይዙ በመጥቀስም የችግሩን አሳሳቢነት አብራርተዋል።
ፈረንሳይ ባዘጋጀችው ለሊባኖስ ድጋፍ የማሰባሰብ አለማቀፍ ጉባኤ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ቴድሮስ፥ የሊባኖስ ሆስፒታሎች በአሁኑ ወቅት ከሚገባው በላይ ተጨናንቀዋል ብለዋል።
ከ2 ሺህ 500 በላይ ሊባኖሳውያንን ህይወት የቀጠፈው እና ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ያቆሰለው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት፥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎችን አፈናቅሏል።
ጦርነቱ በጤና ተቋማት ላይ ያደረሰው ጉዳትም የቆሰሉ ሰዎች በፍጥነት እንዳይታከሙና የህክምና ክትትል ማድረግ የሚገባቸውን ሰዎች ለአደጋ ይጥላል ብለዋል የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም።
በንጹህ ውሃ እጥረት ምክንያት በደቡባዊ ሊባኖስ የኮሌራ ተጠቂ መገኘቱን በመጥቀስም ጦርነቱ ህጻናት ክትባት እንዲያልፋቸው እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የአለም ጤና ድርጅት ከባለፈው አመት ጀምሮ በሊባኖስ የጤና ተቋማት ላይ 53 ጥቃት መድረሱን መዝግቧል። በነዚህ ጥቃቶች 99 ታካሚዎችና የጤና ባለሙያዎች መገደላቸውንም ገልጿል።
የጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች በየትኛውም ጊዜ ከለላ ሊሰጣቸው እንደሚገባ፤ ይህን መተላለፍም አለማቀፍ ስምምነትን እንደመጣስ ቢቆጠርም በጋዛም ሆነ በሊባኖስ የጤና ተቋማት ኢላማ ተደርገው ሲወድሙና ሀኪሞችም ሲገደሉ ታይቷል።
ሲቪሎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ተቁማት ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጠየቀው የአለም ጤና ድርጅት፥ 124 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ሊባኖስ መላኩን በድረገጹ አስነብቧል።
በሊባኖስ እና ጋዛ ተጨማሪ ሞትና ውድመትን ለማስቆም ዋነኛው ግን መድሃኒት ሰላምን ማስፈን መሆኑን በመጥቀስም ለተጎጂዎች በፍጥነት ለመድረስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቅርቧል።