ኢራን 'ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሙቀት' ምክንያት የሁለት ቀናት እረፍት አወጀች
ቴህራን አዛውንቶች እና የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በቤት ውስጥ እንዲቆዩ አሳስባለች
በቅርብ ሳምንታት የሙቀት ማዕበል የተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል
ኢራን በዚህ ሳምንት ረቡዕ እና ሀሙስ ህዝባዊ በዓላት እንደሚሆኑ አስታውቃለች።
ሀገሪቱ "ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሙቀት" እየተናጠች ሲሆን፤ አዛውንቶች እና የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በቤት ውስጥ እንዲቆዩ እንደተነገራቸው የኢራን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘግቧል።
ቀደም ሲል በደቡባዊ ኢራን የሚገኙ በርካታ ከተሞች ለየት ባለ ሙቀት ለቀናት ተቸግረዋል ተብሏል።
በደቡባዊ አህቫዝ ከተማ በዚህ ሳምንት የሙቀት መጠኑ ከ123 ዲግሪ ፋራናይት (51 ሴልሺየስ) መብለጡን መገናኛ ብዙኸን ዘግበዋል።
የመንግስት ቃል አቀባይ አሊ ባሃዶሪ-ጃህሮሚ እንደተናገሩት ረቡዕ እና ሀሙስ በዓላት እንዲሆኑ ተወስኗል።
ቃል አቀባዩ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ሆስፒታሎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ረቡዕ በቴህራን ውስጥ የሙቀት መጠኑ 39 ሴልሺየስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የሙቀት ማዕበሎች በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በትላልቅ የዓለም ክፍሎች ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
ተመራማሪዎች ሰሞነኛ ክስተቶችን በሰዎች ምክንያት ከሚፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር አያይዘዋል።