ኢራን በበኩሏ ለሩሲያ ድሮን የሰጠሁት ከዩክሬን ጦርነት መጀመር በፊት እንደሆነ አስታውቃለች
ኢራን ለሩሲያ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (ድሮን) መስጠቷን አመነች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመራች ዘጠኝ ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ይህ ጦርነት ከዓለም ምግብና ነዳጅ ዋጋ መናር ባለፈ የዲፕሎማሲ መመሰቃቀል አጋጥሟል።
ጦርነቱ በዩክሬን ምድር ይካሄድ እንጂ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከ70 በላይ የዓለማችን ሀገራት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዩክሬን ኢራን ሰራሽ በሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሩሲያ እየተደበደበች መሆኑ ገልጻ ኢራን ከድርጊቷ እንድትታቀብ ስታሳስብ ቆይታለች።
ኢራን በበኩሏ ለሩሲያ ድሮን አለመስጠቷን ክዳ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ለሩሲያ ድሮን መስጠቷን አምናለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሁሴን አሚር እንዳሉት ሀገራቸው ለሩሲያ ድሮን መስጠቷን አምነው ነገር ግን ድሮኖቹ ከዩክሬን ጦርነት መጀመር በፊት የተሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዩክሬን ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ኢራን ለሩሲያ ስለመስጠቷ መረጃ ካላት ይፋ እንድታደርግ ሲሉም ሚንስትሩ አክለዋል።
ዩክሬን በበኩሏ ኢራን ከድሮን በተጨማሪ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል ለሩሲያ ሰጥታለች በሚል ቴህራንን ከሳለች።
ዩክሬን ከ130 በላይ ኢራን ሰራሽ የሆኑ ከሩሲያ የተላኩ ሻሂድ እና ሞሀጀር የተሰኙ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
ኢራን በበኩሏ ለሩሲያ ከድሮን ባለፈ ሚሳኤልም ሆነ ሌላ የጦር መሳሪያ አለመስጠቷን ገልጻለች።
ኢራን ድሮኖቹን ለሩሲያ የሰጠችው በሁለቱ ሀገራት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሰረት እንጂ ዩክሬንን ለመጉዳት እንዳልሆነ አስታውቃለች።
የኢራን ፍላጎት ሩሲያ እና ዩክሬን የጀመሩትን ጦርነት አቁመው ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ እንደሆነም ሚንስትሩ ጠቁመዋል።
ይሁንና ዩክሬን ከኢራንም ሆነ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ መነጋገር አትችልም ያሉት ሚንስትሩ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል።