በኢራን በድንጋይ ከሰል ማውጫ በደረሰ ፍንዳታ የ51 ሰዎች ህይወት አለፈ
ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ከ20 በላይ ሰዎችን ያቆሰለው አደጋ መንስኤ ምርመራ ተጀምሯል ብለዋል
ኢራን በየአመቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል ማዕድን በማውጣት ትጠቀማለች
በኢራን በድንጋይ ከሰል ማውጫ በደረሰ ፍንዳታ በጥቂቱ የ51 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
ከቴህራን በ540 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ታባስ በደረሰው አደጋ 20 ሰዎች መቁሰላቸውንም የሀገሪቱ ብሄራዊ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
ማዳንጆ በተባለ ኩባንያ በሚተዳደረው የድንጋይ ከሰል ማውጫ ውስጥ ፍንዳታው ሲከሰት 71 ሰራተኞች ነበሩ ተብሏል።
አውጪዎች በሚገኙበት ስፍራ የደረሰው ፍንዳታ ከሚቴን ጋዝ አፈትልኮ መውጣት ጋር የተያያዘ ነው መሆኑን የታባስ ግዛት አስተዳዳሪ ሞሀመድ ጃቫድ ቄናት ተናግረዋል።
ቀደም ብለው በወጡ ዘገባዎችም የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉና 17 ሰዎች መቁሰላቸው የተገለጸ ሲሆን፥ 24 ማዕድን አውጪዎች መጥፋታቸው ሲዘገብ ቆይቶ ነበር።
ከጥቂት ስአታት በፊት በወጡት ዘገባዎች ግን ከሚቴን ጋዝ አፈትልኮ መውጣት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ፍንዳታ የ51 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ተመላክቷል፤ አራት ሰዎችንም ከአደጋው ስፍራ በማውጣት ወደሆስፒታል መውሰድ መቻሉ ነው የተገለጸው።
አደጋው የደረሰበት አካባቢ የኢራን 76 በመቶ የድንጋይ ከሰል ምርት የሚገኝበትና ከአስር ግዙፍ ድንጋይ ከሰል አውጪ ኩባንያዎች ስምንቱ የተሰማሩበት መሆኑን የደቡብ ኮራሳን ግዛት አስተዳዳሪ ኣአል አክባር ራሂሚ ተናግረዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ኒውዮርክ ለመጓዝ እየተዘጋጁ የሚገኙት ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን፥ በአደጋው ህይወታቸው ላለፈው ዜጎች ቤተሰቦች መጽናናትን የተመኙ ሲሆን በድንጋይ ከሰል ማውጫው ላይ የደረሰው ፍንዳታ መንስኤ ምርመራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ነዳጅ አምራቿ ኢራን በተለያዩ ማዕድናት ሃብትም የበለጸገች ናት።
ቴህራን በየአመቱ ከምትጠቀመው 3.5 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን የሚሆነውን በራሷ አቅም ትሸፍናለች።
ቀሪውን የድንጋይ ከሰል ከውጭ የምታስገባ ሲሆን አብዛኛው ለብረት አምራች ኩባንያዎች ይውላል ተብሏል።
ኢራን በድንጋይ ከሰል ማዕድን ማውጫዎች ላይ ተደጋጋሚ አደጋዎች አጋጥመዋታል።
በፈረንጆቹ 2009 እና 2013 በደረሱ አደጋዎች የ31 ሰዎች ህይወት ማለፉን ያወሳው የቪኦኤ ዘገባ፥ በ2017ም ጎልቴሳን በተባለው ግዛት በደረሰ ፍንዳታ 42 ማዕድን አውጪዎች መሞታቸውን አስታውሷል።