እስራኤል የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህን በቴህራን ገድላለች ከተባለበት ዕለት ጀምሮ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል
ኢራን እና ሂዝቦላህ ነገ አልያም ከነገ በስቲያ እስራኤልን ሊያጠቁ እንደሚችሉ ተገለጸ።
ከ10 ወራት በፊት ሐማስ በእስራኤል ምድር ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
በጋዛ የተጀመረው ይህ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ወደ ሊባኖስ እና የመን እየተስፋፋ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ በሌሎች አካባቢዎችን ሊሰፋ እንደሚችል ስጋት አይሏል፡፡
በተለይም በኢራን ተመራጩ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ወደ ቴህራን ያመሩት የሐማሱ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ መገደል ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሯል፡፡
ግድያው በግዛቷ የተፈጸመባት ኢራን እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን እስራኤል መቀጣት እንዳለባት እና እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በጉዳዩ ዙሪያ ከቡድን ሰባት ሀገራት ጋር መክረዋል።
ሚንስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ኢራን እና ሂዝቦላህ ነገ አልያም ከነገ በስቲያ ጥቃት ሊከፍቱ ይችላሉ ብለዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ አሜሪካ እና ሌሎች አጋር አካላት የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ወደተባባሰ አለመረጋጋት እንዳይገቡ ስጋት የገባቸው ሲሆን ይህን ለመከላከል የበለጠ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተወያይተዋል ተብሏል።
ኢራን እና እስራኤልን ጨምሮ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አካባቢው እንዲረጋጋ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ቡድን ሰባት አባል ሀገራት ማሳሰባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የእስማኤል ሀኒየህ ግድያ እንዲፈጸም ተሳትፎም ሆነ እውቅና የለኝም ያለችው አሜሪካ ኢራን እስራኤል ካጠቃች ግን ገለልተኛ እንደማትሆን በመከላከያ ሚንስትር ሊዮልድ ኦስቲን በኩል ከሰሞኑ አስታውቃለች፡፡