ቤኔት ቴህራን ምናልባትም በቅርቡ የአውዳሚ አቶሚክ ቦንብ ባለቤት ልትሆን እንደምትችልም አሳስበዋል
ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ እጅግ ተቃርባለች ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ተናገሩ፡፡
ቤኔት ምዕራባውያን ጠንከር ያለ አቋምን ይዘው እርምጃዎችን ካልወሰዱ ቴህራን ምናልባትም በቅርቡ የአውዳሚ አቶሚክ ቦንብ ባለቤት ልትሆን እንደምትችል አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር በነበራቸው የካቢኔ ስብሰባም ይህንኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምዕራባውያን ኢራን ኒውክሌርን ታጥቃ ስጋት ልትሆን እንደምትችል "ነቅተዋል" ሲሉ ለእንግሊዙ ቴሌግራፍ የተናገሩት ቤኔት ብሪታንያ እና ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቿ በቴህራን ላይ የሚያደርጉትን ጫና አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
"ኢራን በማይጠበቅ ፍጥነት ነው ዩራኒዬም እያበለጸገች ያለችው፤ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመታጠቅ ተቃርባለች"ም ብለዋል ቤኔት፡፡
ጠንከር ያለ አቋም ተይዞ እርምጃዎች እስካልተወሰዱ ድረስ ቴህራን ኒውክሌርን ከመታጠቅና የአቶሚክ ቦንብ ባለቤት ከመሆን የሚያግዳት ነገር እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡
እስራኤል ከአሁን በኋላ የሚሰነዘሩባትን የሚሳዔልና ሌሎችንም ጥቃቶች ለመመከት ሁለት ዶላር ብቻ እንደምታወጣ ገለጸች
ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለማምረት በሚያስችላት ደረጃ ዩራኒዬም እያበለጸገች መሆኗ ይነገራል፡፡ ይህን ተከትሎም ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት ንግግር የመጣው፡፡
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቴህራን ባለመተባበሯ ምክንያት ዩራኒዬም የምታበለጽግበትን ሂደት ለመቆጣጠር አልቻልኩም ሲል ይወቅሳል፡፡
በማበልጸጊያ ስፍራዎች የተተከሉ የክትትል ካሜራዎችን ታስተጓጉላለች ሲልም ኤጀንሲው ቴህራንን ይከሳል፡፡
ኢራን በጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ከቋሚ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሃገራትና ከአውሮፓ ህብረት ጋር ወሳኝ የተባለ ስምምነትን አድርጋ ነበር፡፡
ስምምነቱ የምታበለጽገውን የዩራኒዬም መጠን እንድትቀንስ በምላሹም ማዕቀቦች እንዲነሱላት ነበር፡፡ ሆኖም አሜሪካ ራሷን ከስምምነቱ ማስወጣቷን ተከትሎ ውጤታማነቱ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢራንም ለኒውክሌር ምርት የሚሆናትን ዩራኒዬም ማበልጸጓን ቀጥላለች፡፡