ሳዑዲ እና ኢራን በእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ ከገቡ ዓመታትን አስቆጥረዋል
የመካከለኛው ምስራቅ ተቀናቃኞች ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን በኢራቅ ባግዳድ መደራደር ጀመሩ፡፡
ከዓለማችን ነዳጅ ላኪ አገራት መካከል ቀዳሚዎቹ የሆኑት ሳዑዲ እና ኢራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል በኢራቅ ዋና ከተማ በሆነችው ባግዳድ እንደተገናኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ሀያል ለመሆን ፉክክር ላይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሁለቱ ሀገራት በየመን የእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
በየመንና በሶሪያ በተቃራኒ አቅጣጫ ተሰልፈው የተለያዩ አካላትን በማስታጠቅ ጦርነት የገጠሙት ሃገራቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመትም ነበር ለመጀመሪያው ጊዜ የሁለትዮሽ ውይይትን ማድረግ የጀመሩት፡፡ ከወር በፊት ተወያይተው ያደረጉ ሲሆን ኢራን እስካሁን ግልጽ ባላደረገችው ምክንያት ውይይቱን ማቋረጧ ይታወሳል፡፡
ይሁንና ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን በባግዳዱ ወይይት ላይ ስለመሳተፋቸው እስካሁን በይፋ ያወጡት መግለጫ የለም ተብሏል፡፡
የአሁኑ የሁለቱ ሀገራት ውይይት የተካሄደው ሳዑዲ አረቢያ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው 80 ሰዎችን በስቅላት ከቀጣች በኋላ ሲሆን ኢራን በወቅቱ በሞት ከተቀጡት ሰዎች መካከል 41ዱ የሺዓ ዕምነት ተከታዮች መሆናቸውን ገልጻ ድርጊቱን ማውገዟ ይታወሳል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ወዳጅነት የተበላሸው ሳዑዲ በፈረንጆቹ 2016 ላይ የሺዓ ዕምነት መሪ የነበሩትን የሀይማኖት አባት በስቅላት መግደሏን ተከትሎ ነው፡፡
ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለይም በሶሪያ፣ ሊባኖስ እና ኢራቅ ያሉ ተቃዋሚዎችን በመርዳት በተቃራኒ ጎራ በመሰለፍ ይታወቃሉ፡፡