ኢራን ጅነራል ሱሌማኒን ለማሰብ ባዘጋጀችው ስነስርአት ከባድ ፍንዳታ ተከስቶ ሰዎች ሞቱ
ቴህራን “የሽብር ጥቃት ነው” ባለችው ፍንዳታ 73 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉና ከ170 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ተነገሯል
ከእስራኤል ጋር በእጅ አዙር እየተፋለመች ያለችው ኢራን ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ አልገለጸችም
በኢራን ከአራት አመት በፊት በአሜሪካ የአየር ጥቃት በኢራቅ የተገድሉትን ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒን ለማሰብ ባዘጋጀችው ስነስርአት ከባድ ፍንዳታ መከሰቱ ተነገረ።
ቴህራን “የሽብር ጥቃት” ባለችው ፍንዳታ በጥቂቱ የ73 ሰዎች ማለፉና ከ170 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፤ የሟቾቹ ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል።
በጋዛው ጦርነት ከእስራኤል ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ያለችው ቴህራን ከፍንዳታው ወይም የሽብር ጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለበት እስካሁን አልገለጸችም።
የሱሌማኒ ቀብር የሚገኝባት ከርማን ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ ራህማን ጃላሊ የተወሰኑ ሰዎች ከጥቃቱ ለማምለጥ ሲሞክሩ ተረጋግጠው እንደቆሰሉ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ኢራን በቀጠናው ሀገራት የምታደርጋቸውን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በመምራት የምትመካባቸው ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒ በጥር ወር 2020 በአሜሪካ የአየር ጥቃት መገደላቸው የሚታወስ ነው።
የቴህራንን ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማሳደግ የተቋቋመው ቁድስ ሃይል መሪ የነበሩት ሱሌማኒ በሀገራቸው እንደ ብሄራዊ ጀግና ቢታዩም ዋሽንግተን ግን በኢራቁ ጦርነት በርካታ ወታደሮቿ የተገደሉባቸውን የቦምብ ጥቃቶች ማቀናበራቸውን በመጥቀስ ገድላቸዋለች።
እስራኤል በቤሩት ፈጽመዋለች በተባለ የድሮን ጥቃት የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል መሪ ሳሌህ አል አሩሪ መገደላቸውን ተከትሎ ብስጭቷንና ዛቻዋን ያሰማችው ቴህራን በዛሬው ጥቃት ዙሪያ የምትሰጠው መግለጫ እየተጠበቀ ነው።
ኢራናውያንን ክፉኛ አስቆጥቶ የነበረውና ለቀናት ሀዘን ያስቀመጠው የጀነራሉ ግድያ ከህልፈታቸው ከአራት አመት በኋላም የሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ክስተትን ፈጥሯል።
በ2020 ቀብራቸው ሲፈጸም በተፈጠረ መረጋገጥ የ56 ሰዎች ህይወት ማለፉና ከ200 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው የሚታወስ ነው።