የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ ኢራን በእስራኤል ላይ ኃይሏን አሳይታለች አሉ
ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ ባደረሰችው ቀጥተኛ ጥቃት 300 ሚሳይሎች እና ድሮኖችን ያዘነበችው ባለፈዉ ሳምንት ነበር
የእስራኤል እና የኢራን ባላንጣነት ከአስርት አመታት በፊት የጀመረ ቢሆንም ወደ ቀጥተኛ ጦርነት ሲገቡ ግን ይህ የመጀመሪያቸው ነው
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ ኢራን በእስራኤል ላይ ኃይሏን አሳይታለች አሉ።
በእስራኤል ላይ ጥቃት የሰነዘረውን የሀገሪቱን ጦር ያመሰገኑት የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ፣ ኢራን ኃይሏን አሳይታለች ሲሉ ተናግረዋል።
ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ ባደረሰችው ቀጥተኛ ጥቃት 300 ሚሳይሎች እና ድሮኖችን ያዘነበችው ባለፈዉ ሳምንት ነበር።
ኢራን ይህን ጥቃት የሰነዘረችው በሶሪያ ደማስቆ የሚገኘው ኢምባሲዋን በማጥቃት እና ሁለት የሪቮሉሽናሪ ጋርድ ጀነራሎችን ጨምሮ ሰባት ወታደሮችን በመግደል ተጠያቂ ያደረገቻትን እስራኤልን ለመበቀል ነው።
አብዛኞቹ ድሮኖች እና ሚሳይሎች፣ በእስራኤል እና በአጋሮቿ ትብብር እንዲከሽፉ መደረጋቸውን እስራኤል መግለጿ ይታወሳል።
ካሚኒ"ምን ያህል ሚሳይሎች ተወነጨፉ፣ ምንያህሉ ኢላማቸውን መቱ የሚለው ቀደሚ ጥያቄ አይደለም፤ ዋናው ነገር ኢራን በጥቃቱ አቅሟን ማሳየት መቻሏ ነው" ብለዋል።
የኢራንን የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታ ነበር።
ከሶስት ቀናት በፊት እስራኤል ሳታደርሰው አይቀርም በተባለ ጥቃት በኢራኗ ኢስፋን ከተማ ሰማይ ላይ ፍንዳታዎች ተከስተው እንደነበር ተዘግቧል።
ነገርግን ኢራን ጥቃቱን "ሰርጎገቦች" የፈጸሙት ነው በማለት አቃልላ፣ የበቀል እርምጃ የመውሰድ እቅድ እንደሌላትም ገልጻለች።
የኢራን ምላሽ ቀጣናዊ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚለውን ስጋት እንዲቀንስ አድርጎታል።
ካሚኒ"በቅርቡ በተካሄደው ዘመቻ ጦሩ ወጭ በመቆጠብ፣ ትርፍ ማሳደግ ችሏል" ሲሉም ተናግረዋል።
የእስራኤል እና የኢራን ባላንጣነት ከአስርት አመታት በፊት የጀመረ ቢሆንም ወደ ቀጥተኛ ጦርነት ሲገቡ ግን ይህ የመጀመሪያቸው ነው።