ኢራን የኒዩክሌር ፖሊሲዋን ልትቀይር እንደምትችል አስታወቀች
የሀገሪቱ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዥ እስራኤል የደቀነችው ስጋት ቴህራን የቀደመ አቋሟን እንድትለውጥ ሊያደርጋት ይችላል ብለዋል
ኢራን የኒዩክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ግልጋሎት ብቻ የሚውል መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች
ኢራን የኒዩክሌር ፖሊሲዋን ልትቀይር እንደምትችል ገለጸች።
በሀገሪቱ አብዮታዊ ዘብ የኒዩክሌር ደህንነት አዛዡ አህመድ ሃግታላብ፥ ወቅታዊው የእስራኤል የደህንነት ስጋት ቴህራን የቀደመ አቋሟን እንድትለውጥ ያደርጋታል ብለዋል።
ኢራን ኒዩክሌርን ለሰላማዊ ግልጋሎት ብቻ ነው የምጠቀምበት ብትልም ምዕራባውያን ቴህራን አውዳሚ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎችን ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳላት ያምናሉ።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት ለደረሰባት ጥቃት አጻፋውን እመልሳለሁ ማለቷን ተከትሎ ኢራን ሁሉንም የኒዩክሌር ጣቢያዎቿን መዝጋቷ ይታወሳል።
እስራኤል በኢራን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት የምታደርስ ከሆነ ቴህራን በኒዩክሌር ዙሪያ ይዛው የቆየችውን አቋም መቀየሯ እንደማይቀር አህመድ ሃግታላብ መናገራቸውን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
የአብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዦች እስራኤል የአጻፋ እርምጃ ከወሰደች “ታይተው በማይታወቁ መሳሪያዎች ከባድ ምላሽ እንሰጣለን” ማለታቸውም ከኒዩክሌር መሳሪያዎች ጋር ሊያያዝ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
የኢራን የስለላ ድርጅት ሃላፊ በ2021 የምዕራባዊያን ጫና ቴህራንን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን ሊገፋፋት እንደሚችል መናገራቸውንም ሬውተርስ አስታውሷል።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪው አያቶላህ አሊ ካሚኒ ከአምስት አመት በፊት “ኒዩክሌር ቦምቦችን መስራትና መጠቀም በሃይማኖታችን የተከለከለ ነው፤ ምንም እንኳን የኒዩክሌር ቴክኖሎጂው ቢኖራትም አንጠቀመውም” ብለው ነበር።
ኢራን እና አሜሪካ በ2015 የደረሱት የኒዩክሌር ስምምነት በ2018 በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መሰረዙን ተከትሎ ቴህራን የኒዩክሌር ልማቷን ማጠናከሯ ይነገራል።