ኢራን ወታደራዊ በጀቷን በሶስት እጥፍ ልታሳድግ ነው
ቴህራን ከእስራኤል ጋር የገባችበት ፍጥጫ ባየለበት ወቅት ነው ወታደራዊ በጀቷን በ200 በመቶ ለማሳደግ ማቀዷን ያስታወቀችው
የስቶኮልም አለማቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም ኢራን በ2023 ለመከላከያ 10.3 ቢሊየን ዶላር በጀት መድባ እንደነበር ገልጿል
ኢራን የቀጣዩን አመት ወታደራዊ በጀቷን በሶስት እጥፍ ልታሳድግ ነው።
የሀገሪቱ መንግስት ቃልአቀባይ ፋቴህ ሞሃጀራኒ ቴህራን ወታደራዊ በጀቷን በ200 በመቶ ለመጨመር ማቀዷን በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
ቃልአቀባዩዋ የ2024 የሀገሪቱን የመከላከያ በጀት ምን ያህል እንደሆነ ግን አልጠቀሱም።
የስቶኮልም አለማቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም ባወጣው መረጃ ግን የ2023 የኢራን የመከላከያ በጀት 10 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር እንደነበር አስታውቋል።
ቴህራን በ200 በመቶ ወታደራዊ በጀቷን የምታጸድቅ ከሆነ የ2025 የመከላከያ በጀቷ 31 ቢሊየን ዶላር ገደማ ይሆናል ተብሏል።
ረቂቅ በጀቱ በሀገሪቱ ህግ አውጪዎች በመጋቢት ወር 2025 ምክክር ተደርጎበት ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጀርመኑ ዶቼ ቬለ ዘግቧል።
ኢራን ወታደራዊ በጀቷን እንደምታሳድግ ያስታወቀችው በጸጥታው ምክርቤት ስብሰባ ከእስራኤል ጋር የጋለ ክርክር ባደረገች ማግስት ነው።
በምክርቤቱ ስብሰባ አሜሪካ እና እስራኤል ለቅዳሜው ጥቃት ኢራን አጻፋውን እንዳትመልስ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ቴህራን በበኩሏ “በሉአላዊነቴ ላይ ለሚቃጣ ጥቃት አጻፋውን የመመለስ መብት አለኝ” ብላለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት “በእጃችን ያሉትን ሁሉንም መሳሪያዎች እንጠቀማለን” በሚል መዛቱ ይታወሳል።
ኢራን ወቅታዊው ውጥረት በምዕራባውያን ማዕቀብ የተጎዳውን የመከላከያ ሃይሏን ለማጠናከር ወታደራዊ በጀቷን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ እንድታቅድ እንዳደረጋት ተገምቷል።
የመንግስት ቃልአቀባዩዋ ፋቴህ ሞሃጀራኒም “የሀገሪቱን ወታደራዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል” ብለዋል በመግለጫቸው።
የ145 ሀገራትን ወታደራዊ አቅም ደረጃ ያወጣው ግሎባል ፋየርፓወር ኢራንን 14ኛ እስራኤልን ደግሞ 17ኛ ላይ አስቀምጧቸዋል።
610 ሺህ ወታደሮች እና 350 ሺህ ተጠባባቂ ሃይል ያላት ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ጠንካራ ወታደራዊ ሃይል ከገነቡ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትመደባለች።
እስራኤል በበኩሏ 170 ሺህ ወታደር እና 465 ሺህ ተጠባባቂ ጦር እንዳላት የሚጠቅሰው ግሎባል ፋየርፓወር፥ የመከላከያ በጀቷ ግን ከኢራን ከእጥፍ በላይ እንደሚልቅ ጠቁሟል። ቴል አቪቭ በ2024 24.4 ቢሊየን ዶላር መመደቧን በመጥቀስ።