የመካከለኛው ምስራቅ ውዝግብ ከጄነራሉ ወደ አውሮፕላኑ
ከሰሞኑ አሜሪካና ኢራን የጀመሩትና ያባባሱት እሰጥ አገባ ተጋግሎ መሰንበቱ የሚታወቅ ሲሆን ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነኝ በማለቷ ውጥረቱ የረገበ መስሎ ነበር፡፡
በዚህ መሰረትም በፐርሽያ አካባቢ ያለው ችግር መፍትሄ የተገኘለት የበረደም መስሎ ነበር የሚሉ ጸሃፊዎች ነበሩ፡፡
ባሳለፍነው ረቡዕ ንብረትነቱ የቱርክ የሆነ አውሮፕላን ከኢራኗ መዲና ቴህራን ተነስቶ ሲበር መከሰከሱ ይታወሳል በዚህ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ 176 ሰዎች ሞተዋል፡፡
ከሰሞኑ የዚህ አውሮፕላን መከሰከስ መንስኤን ለማወቅ ዓለም የጓጓ ሲሆን አንዳንድ የምዕራብ አገሮች አውሮፕላኑ በኢራን ሳይመታ አልቀረም ሲሉ ሰንብተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ብሪታኒያ ዩክሬን እና ኢራቅ መንግሥታት አውሮፕላኑ በስህተት በሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል ተመትቶ ስለመውደቁ መረጃው አለን ማለታቸው ይታወሳል።
ይሁንና የኢራን ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኃላፊ አሊ አቤደዛዱህ አውሮፕላኑ በምዕራብ አቅጣጫ ከአውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ መብረር ከጀመረ በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ወደ ቀኝ ዞሮ ተመልሶ ለማረፍ እየመጣ ሳለ ነው የተከሰከሰው በማለት ማስተባበያ ሰጥተው ነበር።
ሌሎች የኢራን ሹሞች በበኩላቸው አውሮፕላኑ በኢራን ተመቶ ወድቋል የሚሉ አካላት ከነማስረጃቸው ይምጡ የሚል ክርክር ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡
የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጨምረውም የዓይን እማኞች አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ በእሳት ተያይዞ ማየታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ ትናንት አውሮፕላኑ ከምድር ወደ ሰማይ ተወንጫፊ በሆነ ሚሳኤል ተመትቶ ስለመጣሉ ብዙ የደህንነት መረጃዎች ደርሰውኛል ማለታቸው ሁኔታውን ሌላ አቅጣጫ አስያዘው።ካናዳውያን ጥያቄዎች አሏቸው ለጥያቄዎቻቸውም ምላሽ ማግኘት አለባቸው በማለት በአደጋው ዙሪያ ዝርዝር ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት 176 ሰዎች መካከል 63ቱ ካናዳውያን ሲሆኑ፣ ከዩክሬኗ ኪዬቭ ወደ ቶሮንቶ ካናዳ የሚያቀኑ ነበሩ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ከዚህ አውሮፕላን ጋር በተገናኘ ጥርጣሬ አለኝ። የሆነ አካል ስህተት ሳይሰራ አይቀርም ከማለት ውጪ ዝርዝር ነገር መናገርን አልፈቀዱም ነበር ።
የዩናይት ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንም፣ ሀገራቸው ከካናዳ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ዛሬ ጠዋት ላይ ኢራን ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነውን አውሮፕላን መትቼ ጥዬዋለሁ ስትል ለዓለም አስታወቀች፡፡ ይህንን ያደረገችው ደግሞ በስህተት ስለመሆኑ ነው ይፋ ያሳወቀችው፡፡
ይህ ጉዳይ ከሰሞኑ የአሜሪካና ኢራን ውዝግብ ጋር እንደሚገናኝ በርካቶች እየገመቱ ነው፡፡
ኢራን በአሜሪካ የተገደሉባት የኢራን ጄነራል ጉዳይ ስላበሳጫት ይህንን እርምጃ ወስዳለች የሚሉ መገናኛ ብዙሃና አሉ፡፡ ኢራን በበኩሏ ይህ የሆነው ታስቦበት አይደለም ብላለች፡፡
ሰሞኑን በአሜሪካና ኢራን የተጀመረው የተካረረ እሰጥ አገባ ወደ ድርድርና ንግግር ይመለሳል የሚል ተስፋ የነበረ ቢሆንም የአውሮፕላኑ ግን ነገሩን እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
የኢራን ጦር ባወጣው መግለጫ የዩክሬኑ የመንገደኞች አውሮፕላን ሆነ ተብሎ ሳይሆን በስህተት ተመቷል ይላል፡፡
የጦሩ መግለጫ አውሮፕላኑ በኢራን አብዮታዊ ጥበቃ አቅራቢያ በሚገኙ የደህንነት ቦታዎች እየበረረ ሳለ በስህተት ተመትቶ ነው የተጣለው የሚል ሃሳብ አለው፡፡
በዚህም መሰረት የመንገደኞች አውሮፕላኑ ተመቶ ለመውደቁ ኃላፊነት የሚወስዱት አካላት ተጠያቂ ይሆናሉ ብሏል መግለጫው፡፡
ከጄነራል ኡስማን ሱሌይማኒ መገደል በኋላ ኢራን የአጸፋ ምላሽ አሰጣለሁ ማለቷና በኢራቅ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መሰንዘሯ የሚታወስ ሲሆን አውሮፕላኑንም መትታ የጣለችውም በተመሳሳይ ቀን ነው፡፡
ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው ይህ ሁሉ እሰጣ ገባ የጀመረው አሜሪካ በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ ጄነራል ቃሲም ሱሌይማኒን ከገደለች በኋላ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ፣ ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒን አሸባሪ ይበሉት እንጂ በኢራናውያን ዘንድ እንደ ጀግና ነበር የሚቆጠሩት።
የጄነራል ቃሲም መገደል የዩክሬን አውሮፕላን መከስከስ ቀጣናውን ወደለየለት የግጭትና የትርምስ ቦታ እንዳያመራው ተሰግቷል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን