በኢራን የፓርላማ ምርጫ የተመዘገበው የመራጮች ቁጥር ከ1979 ወዲህ ዝቅተኛው ነው ተባለ
መምረጥ ከሚችሉት ኢራናውያን መካከል ድምጽ የሰጡት 40 በመቶ ወይም 25 ሚሊየን ብቻ መሆናቸው ተነግሯል
15 ሺህ እጩዎች 290 መቀመጫ ላለው የኢራን ፓርላማ ተፎካክረዋል
ኢራን በትናንትናው እለት ያካሄደችው የፓርላማ ምርጫ የመራጭ ድርቅ የመታው እንደነበር ተገለጸ።
ድምጽ መስጠት ከሚችሉ ዜጎች መካከል ወደ ምርጫ ጣቢያ ያመሩት 40 ከመቶ ወይም 25 ሚሊየን ብቻ መሆናቸውን ሃማሻህሪ የተሰኘው የኢራን ጋዜጣን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
ይህም ምርጫው ከ1979ኙ የኢራን አብዮት በኋላ ዝቅተኛ መራጭ የተመዘገበበት እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል።
የኢራን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር በዛሬው እለት በምርጫው ምን ያህል ሰዎች መሳተፋቸውን በይፋ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የሀገሪቱ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ኢራናውያን ድምጽ በመስጠት የሀገሪቱን ጠላቶች እንዲያሳፍሩ ጥሪ ቢያቀርቡም የተጠበቀውን ያህል ህዝብ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አላመራም።
የኖቬል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ናርጀስ ሞሀመዲን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎች ኢራናውያን “በይስሙላ” ምርጫው ድምጽ እንዳይሰጡ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
15 ሺህ እጩዎች 290 መቀመጫ ባለው የኢራን ፓርላማ ለመግባት በተፎካከሩበት ምርጫ ለውጥ የሚያቀነቅኑ እጩዎች እንዳይካተቱ ተደርጓል የሚል ወቀሳም ሲቀርብ ቆይቷል።
የማሻ አሚኒ ግድያን ተከትሎ ከተቀሰቀሱ አመጾች በኋላ የተካሄደው ምርጫ 88 መቀመጫዎች ላሉት የባለሙያዎች ምክርቤትም ድምጽ የተሰጠበት ነው።
የባለሙያዎች ምክርቤቱ የ84 አመቱን አያቶላህ አሊ ሃሚኒ የሚተኩ ሃይማኖታዊ መሪን የመምረጥ ሃላፊነት ተጥሎበታል።
በኒዩክሌር ፕሮግራሟ ምክንያት በምዕራባውያን በርካታ ማዕቀቦች የተጣሉባት ቴህራን፥ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ያላት ተሳትፎ ምጣኔ ሃብቷን ይበልጥ እንዳይጎዳው ተሰግቷል።
ሃማስን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች የምትባለው ኢራን ግን ከትናንቱ ምርጫም ሆነ ከኢኮኖሚዋ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች “ጠላቶቼ” የምትላቸው ሀገራት የሚነዟቸው ውዥንብሮች ናቸው ባይ ናት።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በፓርላማ ምርጫው ሚሊየኖች ድምጽ መስጠታቸውን ለማሳየት ቢሞክሩም ቴህራንን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ላይ ሰልፍ የማይታይባቸውና ጭር ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች ነበሩ ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።