በኢራን ይደገፋል የተባለው ካታይብ ሄዝቦላህ በዮርዳኖስ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮችን መግደሉ ይታወሳል
አሜሪካ በኢራቅና ሶሪያ የሚገኙ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና የሚደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖችን መደብደቧን አስታወቀች።
ጥቃቱ ባለፈው ሳምንት በዮርዳኖስ በድሮን ጥቃት ለተገደሉ ሶስት አሜሪካውያን ወታደሮች የአጻፋ እርምጃ መሆኑን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ በተፈጸሙት የአየር ጥቃቶች ከ85 በላይ የቡድኖቹ ይዞታዎች መመታታቸውንም ነው ፔንታጎን ያስታወቀው።
የሶሪያ ብሄራዊ የዜና ወኪል ሳና “የአሜሪካ ወራሪ ሃይል” በሀገሪቱ በርሃማ አካባቢዎች እና ከኢራቅ በሚያዋስነው ድንበር በፈጸማቸው ጥቃቶች በርካታ ጉዳት ደርሷል ብሏል።
የኢራቅ ጦርም የዋሽንግተን እርምጃ የባግዳድን ሉአላዊነት የተዳፈረና ቀጠናውን ወደባሰ ብጥብጥ የሚከት ነው በሚል ተቃውሞውን አሰምቷል።
ባለፈው ሳምንት በጆርዳን ሶስት ወታደሮቿ የተገደሉባትና ከ40 በላይ ወታደሮች የቆሰሉባት አሜሪካ ግን የአየር ጥቃቱ እንደሚቀጥል አስታውቃለች።
“ይሄ ጅማሮ ነው፤ የአጻፋ እርምጃችን ይቀጥላል” ያሉት የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን፥ ከኢራን ጋር ጦርነት አንፈልግም ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ የባይደን አስተዳደር ለወታደሮቹ ግድያ ሃላፊነት የወሰደውን ካታይብ ሄዝቦላህ በምትደግፈው ቴህራን ላይ የቀጥታ እርምጃ እንዲወስድ ሪፐብሊካኖች ጫና እያደረጉ ነው ተብሏል።
የትናንቱ የአጻፋ እርምጃ ከወታደሮቹ ግድያ ከአንድ ሳምንት በኋላ መፈጸሙም ታጣቂዎቹ እንዲደበቁ አድርጓል የሚል ትችት እያስከተለ ነው።
ከጥቃቱ በፊት አስተያየታቸውን የሰጡት የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ጦርነት እንደማትሻ እና “ለሚተነኩሳት ግን ጠንካራ አጻፋዊ እርምጃ” እንደምትወስድ መናገራቸውን ኢርና አስነብቧል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን የገለጹ ታጣቂ ቡድኖች በኢራቅ፣ ሶሪያና ዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ከ160 በላይ የጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸው ተገልጿል።
አሜሪካ በኢራቅ 2 ሺህ 500:፥ በሶሪያ ደግሞ 900 ወታደሮች እንዳሏት ይታወቃል።