ኢራን እና የአውሮፓ ህብረት በቴህራን የኑክሌር መርሃግብር ዙሪያ ንግግር እያካሄዱ ነው ተባለ
ሰኞ እለት የተካሄደው ንግግር ባለፈው ህዳር ወር የነበረውን ውይይት ተከትሎ የመጣ ነው
ኢራን "ሁለቱም ወገኖች ድርድር መጀመር እንደሚያስፈልግና ስምምነት ላይ ለመድረስ ሁሉም አካላት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና መጠበቅ እንዳለባቸው" ተስማምተዋል ብለዋል
ኢራን እና የአውሮፓ ህብረት በቴህራን የኑክሌር መርሃግብር ዙሪያ ንግግር እያካሄዱ ነው ተባለ።
ኢራን፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በአወዛጋቢው የቴህራን የኑክሌር መርሃግብር ዙሪያ ንግግር እያካሄዱ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"ንግግሮቹ እውነተኛ፣ ግልጽና ገንቢ ነበሩ። ማዕቀብ በማንሳት እና በኑክሌር ጣቢያዎች ዙሪያ በሚያጠነጥኑ ሃሳቦች ላይ ተወያይተናል"ሲሉ የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ገርባባዲ በኤክስ ገጻቸው በትናንትናው እለት አስፍረዋል።
ገሪባባዲ አክለውም "ሁለቱም ወገኖች ድርድር መጀመር እንደሚያስፈልግና ስምምነት ላይ ለመድረስ ሁሉም አካላት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና መጠበቅ እንዳለባቸው ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል።ንግግሩን ለመቀጠል ተስምተናል" ብለዋል።
ሰኞ እለት የተካሄደው ንግግር ባለፈው ህዳር ወር የነበረውን ውይይት ተከትሎ የመጣ ነው። በወቅቱ የኢራን ባለስልጣን ከአውሮፓውያን ጋር ያለውን ፍኖተ ካርታ ማጠናቀቅ "የኑክሌር ስምምነቱን ለመግደል ወይም እንዲያንሰራራ ለማድረግ ኳሷ አሜሪካ ሜዳ ውስጥ እንድታርፍ ያደርጋል" ብለው ነበር።
በ2ዐ18 በዶናልድ ትራምፕ የምትመራው አሜሪካ በ2015 ከተደረሰው የኑክሌር ውል ስትወጣ ሌሎች ስድስት ኃያላን ሀገራት ደግሞ በኢራን ላይ ከባድ ማዕቀብ በድጋሚ ጥለውባታል። ይህን ተከትሎ ኢራን የዩራኒየም ክምችት በማሳደግ፣ የመቀጣጠል አቅሙን በመጨመር እና ዘመናዊ ጣቢያ በማቋቋም እና በመሳሰሉት ተግባራት ውሉን ስትጥስ ተስተውላለች።
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደርና ቴህራን ውሉን በድጋሚ እንዲያንስራራ ለማድረግ ያደረጉት ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር ሳይሳካ ቀርቷል።
ትርምፕ ከዚህ በፊት በስልጣን በነበሩበት ወቅት ኢራንን በኢኮኖሚ በማዳከም በኑክሌርና በባለስቲክ ሚሳይል መርሃግብሮቿ እና በቀጣናዊ እንቅስቃሴዎቿ ላይ ስምምነት ላይ እንድትደርስ ለማድረግ ሲጠቀሙት የነበረውን ፖሊሲያቸውን እንደሚያስቀጥሉት ዝተዋል።