ሰሜን ኮሪያ በርካታ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች
ፒዮንግያንግ በ2025 ለሁለተኛ ጊዜ ሚሳኤሎችን ያስወነጨፈችው ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ከመግባታቸው በፊት መልዕክት ለመስደድ ነው ተብሏል
የዛሬው የሚሳኤል ሙከራ በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለሩሲያ የሚላኩ ሚሳኤሎችን ለመፈተሽ ያለመ ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል
ሰሜን ኮሪያ በርካታ አጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ ጦር ገለጸ።
ጋንጊ ከተባለው የሰሜን ኮሪያ አካባቢ የተወነጨፉት ሚሳኤሎች 250 ኪሎሜትሮች ከተጓዙ በኋላ በጃፓን ባህር ውስጥ መግባታቸውንም አስታውቋል።
ፒዮንግያንግ የሚሳኤል ሙከራውን ያደረገችው የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታኬሺ ኢዋያ በሴኡል ጉብኝት ማድረግ በጀመሩበት ወቅት ነው።
የደቡብ ኮሪያ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ቾይ ሳንግ ሞክ የሚሳኤል ሙከራው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳብን የተጣረሰ ነው በሚል አውግዘውታል።
"ሴኡል ለሰሜን ኮሪያ ጸብ አጫሪ ድርጊት ከአጋሯ አሜሪካ ጋር በመተባበር ጠንካራ አጻፋዊ ምላሽ ትሰጣለች" ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ተንታኞች በዛሬው እለት የተካሄደው የሚሳኤል ሙከራ የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር በቀጣይ ሳምንት ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለሚገቡት ዶናልድ ትራምፕ መልዕክት የላከበት ነው ያላሉ።
ሰሜን ኮሪያ የፈረንጆቹ አዲስ አመት 2025 ከገባ ወዲህ ሁለተኛውን የሚሳኤል ሙከራ ነው ያደረገችው። ባለፈው ፒዮንግያንግ ሳምንት አዲስ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሴኡል ጉብኝት ሲያደርጉ የተወነጨፈው አዲስ ሚሳኤል ዋሽንግተን እና ሴኡልን ጨምሮ የቀጠናው አጋሮቻቸውን አሳስቧል።
ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብሯን ማሳደጓን ያነሱት ብሊንከን፥ ሀገራቱ በስፔስ ቴክኖሎጂም በቅርበት እየሰሩ ነው ማለታቸውን ፍራንስ 24 አስታውሷል።
ፒዮንግያንግ በዛሬው እለት ያደረገችው ሙከራም በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለሩሲያ የሚላኩ ሚሳኤሎችን ለመፈተሽ ያለመ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ዩክሬን ከ10 ሺህ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ ተሰማርተው በዩክሬኑ ጦርነት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ያምናሉ። ሞስኮም ሆነች ፒዮንግያንግ ግን እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።
የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋምን የጠቀሱ የሀገሪቱ የምክርቤት አባል 300 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መገደላቸውንና ከ2 ሺህ 700 በላዩ መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም ሁለት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ ኩርስክ ክልል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በሳምንቱ መጨረሻ ተናግረው ነበር።
የተማረኩትን የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ለመልቀቅ ሩሲያ የያዘቻቸውን የዩክሬን ወታደሮች መፍታት እንዳለባት መግለጻቸውም አይዘነጋም።