ኢራን ባለፈው አመት 834 ሰዎችን በስቅላት መቅጣቷ ተነገረ
የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፥ ቴህራን የሞት ቅጣትን እንደማስፈራሪያ እየተጠቀመች ነው በሚል ወቅሰዋል
በ2023 በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር ከ2015 ወዲህ ከፍተኛውና ከ2022ቱ በ43 በመቶ ብልጫ ያለው ነው ተብሏል
ኢራን ባለፈው የፈርንጆች አመት ከ800 በላይ ሰዎችን በስቅላት መቅጣቷ ተነገረ።
በ2023 የተመዘገበው የሞት ቅጣት ከ2015ቱ (972) በመቀጠል ከፍተኛው ነው የተባለ ሲሆን፥ ከ2022 በ43 በመቶ ብልጫ ማሳየቱም ተጠቁሟል።
በኖርዌይ የሚገኘው የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም “አይኤችአር” እና ተቀማጭነቱን ፓሪስ ያደረገው የሞት ቅጣትን የሚቃወም ድርጅት “ኢሲፒኤም” በዛሬው እለት የጋራ ሪፖርታቸውን አውጥተዋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ በሪፖርታቸው በኢራን በ2023 834 ሰዎች በስቅላት መቀጣታቸውን አመላክተዋል።
ማሻ አሚኒ በ2022 በጸጥታ ሃይሎች ከተገደለች በኋላ በኢራን ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በርካቶች የሞት ቅጣት ተላልፎባቸው ተፈጻሚ ሆኗል ብሏል ሪፖርቱ።
ዘጠኝ ሰዎች በ2022ቱ ተቃውሞ ወቅት በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት በማድረስ ጥፋተኛ ተብለው በሞት ተቀጥተዋል፤ 471 ሰዎች ደግሞ ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ በስቅላት ተቀጥተዋል ብሏል ሪፖርቱ።
በሞት ከተቀጡት ውስጥ 167ቱ በደቡብ ምስራቅ ኢራን የሚገኙ የባሉቺ ጎሳ አባላት መሆናቸውም ነው የተጠቀሰው።
አብዛኞቹ የስቅላት ቅጣቶች በማረሚያ ቤቶች መፈጸማቸውን የገለጹት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ፥ የሰባት ሰዎች ስቅላት በአደባባይ መፈጸሙን አውስተዋል።
በሞት የተቀጡት ሴቶች ቁጥርም 22 መሆኑንና በአስር አመት ውስጥ ከፍተኛው መሆኑንም ያወጡት ሪፖርት ጠቁሟል።
ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ሪፖርት ምላሽ ያልሰጠችው ቴህራን፥ በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ያደረገችው አሃዝ በሪፖርቱ ከተጠቀሰው 15 በመቶውን ብቻ ነው መባሉንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ድርጅቶቹ ኢራን የሞት ቅጣትን እንደ ማስፈራሪያ መጠቀሟን መቀጠሏንና አለማቀፍ ተቋማትም ዝምታን መምረጣቸው ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
“በማህበረሰቡ ውስጥ ፍርሃት መንዛት የአገዛዙ በስልጣን መቆያ ብቸኛ መንገድ ነው፤ ለዚህም የሞት ቅጣትን ዋነኛ መሳሪያ አድርገውታል” ብለዋል የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም “አይኤችአር” ዳይሬክተር ማህሙድ አሚሪ ።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ተቋም ኢራን ከ2022ቱ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሰዎችን እንዳትገድል መጠየቁ ይታወሳል።
ቴህራን ግን ከሞት ቅጣት ጋር ተያይዞ የሚቀርቦ ወቀሳዎች “ፖለቲካዊ ሸፍጥ” ያለባቸው ናቸው በሚል ውድቅ ስታደርግ መቆየቷን ፍራንስ 24 አስነብቧል።