ኢራን ለእስራኤል ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸውን 4 ሰዎች በስቅላት ቀጣች
የሞሳድ የስለላ መረብ አባል ነበሩ የተባሉት ግለሰቦች ትናንት ጠዋት ነው በስቅላት የተቀጡት
ሌሎች ሶስት ግለሰቦችም ከ5 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል
ኢራን ለእስራኤል ሲሰልሉ ደርሼባቸዋለው ያለቻቸውን 4 ሰዎች በስቅላት መቅጣቷ ተነገረ።
የሞሳድ የስለላ መረብ አባል ነበሩ የተባሉት ግለሰቦች ትናንት ጠዋት መገደላቸውን ሜህር የተባለው የኢራን የዜና ወኪል ዘግቧል።
በስቅላት የተገደሉት ሰዎች በስለላ እና ጠለፋ ወንጀል እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን በመስራት ተከሰዋል።
ለስለላ ስራቸውም በውጭ ምንዛሬ ገቢ ይደረግላቸዋል የሚለው በክሱ ተካቷል።
ግለስቦቹ የይግባኝ መብታቸውን ሳይከበር የኢራን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰሞኑ በተከሳሾቹ ላይ የተላለፈውን የሞት ቅጣት በማጽደቁ ቅጣቱ በስቅላት ተፈጻሚ ሆኗል።
የኢራንን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ እንደጣሉ የታመነባቸው ሌሎች ሶስት ግለሰቦችም ከ5 እስከ 10 አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ነው የተገለጸው።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መርጃ እንደሚያሳየው ኢራን በ2021 ብቻ 314 ስዎችን በስቅላት ቀጥታለች።
ይህም በመላው መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተፈጸመው በእጥፍ ይበልጣል ነው የተባለው።
እስራኤልና ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ በአየነ ቁራኛ የሚተያዩ ሀገራት ናቸው።
ቴህራን ከ1979ኙ አብዮት በኋላ የእስራኤልን ሉአላዊነት እንደማትቀበል ያሳወቀች ሲሆን እንደ ሄዝቦላህ እና ሃማስ ያሉ ጸረ እስራኤል አቋም ያላቸው ቡድኖች ትደግፋለች።
ሁለቱ ሀገራት በስለላ እርስ በርስ ይወነጃጀላሉ።
እስራኤል ባለፈው ጥር ወር የኢራንን የስለላ ቡድን ተልዕኮ ማክሸፏን መግለጿ ይታወሳል።