ከአሜሪካ ጋር መደራደር ኢራን አሁን የገባችበትን ችግር አይፈታውም - አያቶላህ አሊ ካሚኒ
ካማኒ አሜሪካ ከቴህራን ጋር ለመደራደር የምታስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አያቀራርቡም ብለዋል
ካሚኒ በስም ባይጠቅሷትም አሜሪካን ቀንደኛ ጠላታችን ናት ሲሉ ባለፈው ተናግረዋል
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ከአሜሪካ ጋር ድርድር ማድረግ ወቅታዊ የኢራንን ችግር አይፈታውም አሉ።
ሃይማኖታዊ መሪው በኢራኑ አብዮታዊ ዘብ ከሚመሩ ወዶገብ ታጣቂዎች ጋር መክረዋል።
በመስከረም ወር የ22 አመቷ ማሻ አሚኒ ከተገደለች በኋላ ኢራን በተቃውሞ እየተናጠች ነው።
ለተቃውሞ የወጡ ከ300 በላይ ኢራናውያን በፀጥታ ሃይሎች መገደልም ቁጣውን እያባባሰው ይገኛል።
የሀገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት አመፁን እያፋፋሙት ያሉት ምዕራባውያን ናቸው ይላሉ።
አያቶላህ አሊ ሃሚኒም ከታጣቂዎቹ ጋር በነበራቸው ቆይታ "አንዳንዶች አሁን ላይ ሀገራችን ላይ የተጋረጠውን ችግር ከአሜሪካ ጋር በመደራደር አስቁሙት ይሉናል፤ ይህ ግን በፍፁም አይሆንም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዋሽንግተን ጋር የሚደረገው ድርድር ምንም መፍትሄን ይዞ እንደማይመጣም ነው ያብራሩት።
"አሜሪካ ተቃውሞው እንዲረግብ የምታስቀምጣቸው ቅደመ ሁኔታዎች ሊያግባቡን አይችሉም፤ ኢራን የኒዩክሌር ፕሮግራሞን ታቋርጥ፣ ህገመንግስቷን ታሻሽል፣ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዎቿን ትዝጋ እና የውጭ ሀገራት ተፅዕኖዋን ትግታ የሚሉት ቅድመ ሁኔታዎች በፍፁም ልንቀበላቸው አንችልም" ነው ያሉት ሃሚኒ።
የኢራኑ ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒ በባግዳድ አሜሪካ በድሮን ከገደለችው በኋላ ኢራናውያን አደባባይ በመውጣት ለአሜሪካ ያላቸውን አመለካከት በገሃድ አንፀባርቀዋል ያሉት ሃይማኖታዊ መሪው፥ ይህ የብዙሃን ኢራናውያን ድምፅ ሊደመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሁለተኛ ወሩን በያዘው የአደባባይ ተቃውሞ እየተሳተፉ ያሉት ተገቢው እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ በመግለፅም ችግሩ አደባባይ በወጡ "ጥቂት አመፀኞች" የመጣ አይደለም ብለዋል።
ሃሚኒ የጦርነት አውድማው ሰፊ ባለድርሻዎች እንዳሉት ጠቅሰው፤ "ትልቁ ፀባችን ከአለም አቀፍ ትዕቢተኞች ጋር ነው" ሲሉም ነው እነ አሜሪካን እና እስራኤልን ስም ሳይጠቅሱ በነገር ወረፍ ያደረጉት።
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲም በቴህራን የሚገኘውን የበጎፈቃደኛ ሚሊሻዎች ቡድን (ባሲጅ) ከጎበኙ በኋላ ለተቃውሞ በሚወጡ ኢራናውያን ላይ እርምጃው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሚሊሻዎቹ ተቃዋሚዎች ላይ የወሰዱትን እርምጃም ማድነቃቸውን ነው የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል ያስነበበው።