ፖርቹጋላዊው ኮከብ ሮናልዶ “ለአል-ናስር መፈረሜ በህይወቴ የምኮራበት ውሳኔ ነው” አለ
አዲሱ የሮናልዶ ክለብ አል ናስር የሳዑዲ ፕሮ ሊግን ዘጠኝ ጊዜ ማሸነፍ የቻለ አንጋፋ ክለብ ነው
የአል ናስር አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ሩዲ ጋርሽያ፤ ሮናልዶን በሳዑዲ ፕሮ ሊግ መመልከት " የሚደንቅ ነው "ብለዋል
ፓርቹጋላዊው ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስትር ቤት ከተፈጠረው ውዝግብ በኋላ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ ለሳዑዲ አረቢያው ክለብ አል ናስር መፈረሙ ይታወቃል፡፡
የ37 ዓመቱ ኮከብ ከቤተሰቦቹ ጋር ሰኞ ሌሊት ሪያድ ሲገባ የክለቡ ፕሬዝዳንት ሙሳሊ አል ሙአመር፣ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አብዱላህ ቢን አብዱራሂም አል ኦምራኒን ጨምሮ የክለቡ ከፍተኛ አመራሮች ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።
ሮናልዶ በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገረው ወደ ሳዑዲ ከማቅናቱ በፊት የተለያዩ ክለቦች ጥያቄ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም የሳዑዲ አረቢያው ክለብ አል ናስር ምርጫው ማድረጉ ተናግረዋል፡፡
ከብራዚል፣ አውስትራልያ፣ አሜሪካን እና ፖርቱጋል ክለቦች ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር ያለው የ37 ዓመቱ ሮናልዶ ፤ "እኔ ግን ለአል-ናስር የገባሁት ቃል ማክበር ወደድኩኝ" ብሏል፡፡
"ታላለቅ በሚባሉ የአውሮፓ ክለቦች ተጫውቼ አሸንፌያለሁ፤ አሁን ደግሞ አዲስ የእስያ ልምድ ለማግኘትና ፈተናዎችን ለመጋፈጥ መጥቻለሁ" ሲልም አክሏል፡፡
“በሕይወቴ ውስጥ ይህን ትልቅ ውሳኔ በመወሰኔ ኩራት ይሰማኛል” ሲልም ተናግረዋል የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ሮናልዶ፡፡
ፖርቹጋላዊው ከአል ናስር ጋር የገባው ውል በዓመት 177 ሚሊዮን ፓውንድ እየተከፈለው እስከ 2025 ከክለቡ ጋር እንዲቆይ የሚያስችለው ነው፡፡
የገንዘቡ መጠን የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊውና ፖርቹጋላዊው እግር ኳስ ጠቢብ በእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛ ተከፋይ እንዲሆን ያስቻለ ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ የሮናልዶ ክለብ አል ናስር የሳዑዲ ፕሮ ሊግን ዘጠኝ ጊዜ ማሸነፍ የቻለ አንጋፋ ክለብ ነው፡፡
ከአል ናስር የቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን በሳዑዲ ሊግ ሊያሳካው ስለሚያስበው ስኬት የተጠየቀው ሮናልዶ፡ "እዚህ ሀገር ያለው ሊግ እጅግ ተወዳዳሪ መሆኑ አውቃለሁ፣ በርካታ ጨዋታዎችም ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ስለዚህም ከአሁን በኋላ አሰልጣኜ ተጫወት ባለኝ ጊዜ ለማጫወት ዝግጁ ነኝ" ሲል ተናግሯል፡፡
ለሳዑዲ አረቢያ አዲሱ ትውልድ የራሴን የሆነ አሻራ ትቼ ማለፍ እፈልጋሉም ብሏል ሮናልዶ፡፡
የአል ናስር ክለብ አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ሩዲ ጋርሽያ፤ የሮናልዶ ለአል ናስር ክለብ መፈረም ለሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ አስፈላጊ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
እንደ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የመሰሉ የተሟላ ክህሎት ያላቸው ተጨዋቾች በሳዑዲ ፕሮ ሊግ መመልከት " የሚደንቅ ነው "ም ብለዋል፡፡
"ዋና ዓላማዬ ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ ጋር በመሆን አል ናስር ዋንጫ እንዲወስድ ማድረግ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
ሮናልዶ ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ ወደ አል-ናስር ሜዳ በማቅናት በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ የክለቡ ደጋፊዎች ጋር ተዋውቋል፡፡