ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “አይሁዶች ወራሪዎች አይደሉም” ብለዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) እስራኤል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶችን በ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፍርድ ቤቱን የጠየቀው የእስራኤልን “ወረራ፣ ሰፈራ እና መቀላቀል... የቅድስት እየሩሳሌም የስነ ህዝብ ስብጥርን፣ ባህሪን እና ደረጃን ለመለወጥ የታቀዱ እርምጃዎችን የምክር አስተያየት እንዲሰጥ” የሚል ነው፡፡
የተመድ ጉባኤ ያቀረበው ጥያቄ ፍልስጤምን ቢያስደስትም እስራኤልን ቅር አሰኝቷል፡፡
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ ቃል አቀባይ ነቢል አቡ ሩዲነህ የጉባኤውን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት መግለጫ “እስራኤል በህግ የምትተዳደር ሃገር የምትሆንበት እና በህዝባችን ላይ ለፈጸመችው ጥፋት ተጠያቂ የምትሆንበት ጊዜ ደርሷል” ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በውሳኔው የተቆጡት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተባበሩት መንግስታት ድምጽ የሚገደብ ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የተመድ ውሳኔ “የተናቀ ነው” ሲሉ ያጣጣሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት “የአይሁድ ሕዝብ በገዛ ምድራቸው ላይ ወራሪዎች አይደሉም ወይም በዘላለማዊው ዋና ከተማችን እየሩሳሌም ውስጥ ወራሪዎች አይደሉም እናም የትኛውም የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ያንን ታሪካዊ እውነት ሊያጣምም አይችልም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
እስራኤል ዌስት ባንክን ፣ጋዛን እና ምስራቅ እየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው በ 1967 ጦርነት እንደበር አይዘነጋም፡፡
ያም ሆኖ እስራኤል ያዘቻቸው ቦታዎች በፍልስጤም የይገባኛል ጥያቄ የሚቀርብባቸው እንደመሆናቸው የማቋርጡ ግጭቶችን ለማስቆም በሀገራቱ መካካል ረጅም አመታት የፈጀ የሰላም ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ብዙ የተደከመበት የሰላም ድርድር እንደፈረንጆቹ 2014 መፍረሱ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ አዲሱ የእስራኤል መንግስት በዌስት ባንክ ውስጥ የሚያከናውነውን ሰፈራ ለማጠናከር ቃል መግባቱ ውጥረቱ ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡