በእስራኤል የሚሳኤል ጥቃት የደማስቆ ኤርፖርት ከአገልግሎት ውጭ ሆኗል - ሶሪያ
በደቡባዊ ሶሪያ በተፈጸመ ሌላ ጥቃትም ሁለት የሶሪያ ወታደሮች መገደላቸውን የሶሪያ ጦር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አመላክቷል
በሶሪያ የኢራን ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የፈጸመችው እስራኤል ስለዛሬው ጥቃት ምላሽ አልሰጠችም
በሶሪያ መዲና የሚገኘው የደማስቆ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በእስራኤል የሚሳኤል ጥቃት ከአገልግሎት ውጭ መሆኑንቭ የሶሪያ ጦር ገለጸ።
ሚሳኤሉ ከእስራኤሏ ቲበሪያስ ሀይቅ መነሳቱንም ነው የጦሩ መግለጫ ያመላከተው።
በደቡባዊ ሶሪያ በተፈጸመ ሌላ ጥቃትም ሁለት የሶሪያ ወታደሮች መገደላቸውና ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ ወታደሮች መቁሰላቸው ተገልጿል።
የደህንነት ምንጮች ግን ጥቃቱ የኢራን ቁድስ ሃይል የሚገኝበትን አውሮፕላን ማረፊያ ኢላማ ያደረገ ስለመሆኑ መጠቆማቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
በሶሪያ የበሽር አል አሳድ መንግስትን የሚደግፉ የኢራን ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የፈጸመችው እስራኤል ስለዛሬው ጥቃት ምላሽ አልሰጠችም።
እስራኤል ባለፈው የፈረንጆቹ አመት በሶሪያ እና ሊባኖስ ከኢራን የሚቀርቡ የመሳሪያ ድጋፎችን ለመግታት በደማስቆና ሌሎች አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ጥቃት ማድረሷ ይታወሳል።
በደምስቆ አውሮፕላን ማረፊያ በሰኔ ወር 2022 ሁለት የአየር ጥቃቶችን በመፈጸሟ አውሮፕላን ማረፊያው አገልግሎቱን አቋርጦ መቆየቱም በዘገባው ተወስቷል።
እስራኤል በሰሜናዊ ሶሪያ በሚገኘው የአሌፖ አውሮፕላን ማረፊያም ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽማ ለቀናት ከአገልግሎት ውጭ መሆኑ አይዘነጋም።
ቴህራን በሲቪል አውሮፕላን ማረፊያዎች በኩል የጦር መሳሪያዎችን ለሶሪያ ታጣቂዎች እያቀረበች ነው በሚል ነው ቴል አቪቭ ጥቃቶቹን የምትፈጽመው።
በሶሪያ ጦርነት የእጅ አዙር ፍልሚያው በ2013 ነው የተጀመረው።
በወቅቱ ሶሪያ ከሩስያ ያገኘችውን ኤስ ኤ 17 የአየር መቃወሚያ ለሊባኖሱ ሄዝቦላህ አሳልፋ ለመስጠት ስትሞክር እስራኤል የአየር ጥቃት መፈጸሟን ትገልጻለች።
ኢራን ሄዝቦላህን ጨምሮ በሶሪያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን እንደምትደግፍ በእስራኤል በኩል ተደጋግሞ ቢጠቀስም የበሽር አል አሳድ መንግስት በይፋ ማረጋገጫ ስጥቶ አያውቅም።
የኢራን ወታደራዊ አማካሪዎች በሶሪያ መገኘታቸውን ከመጥቀሳቸው ውጭ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት የቴህራንን ተሳትፎ አንስተው አያውቁም።
እስራኤል ግን በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎችን እና የጦር መሳሪያ ዝውውሩን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እየፈጸመች ነው ተብሏል።