የኢራን ብሄራዊ ቴሌቪዥን መደበኛ ስርጭቱን አቋርጦ ሙሉ ትኩረቱን አደጋው ላይ አድርጓል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሄሊኮፕተር ግጭት አደጋው ከባድ ጉዳት ሳይገጥማቸው እንዳልቀረ እየተነገረ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ከአዘርባጃን በምትዋሰነው የኢራን የድንበር ከተማ ግድብ መርቀው ሲመለሱ የተሳፈሩበት ሄሊኮፕተር ከተራራ ጋር መጋጨቱ ከተገለጸ ወዲህ አለም ትኩረቱን በቴህራን ላይ አድርጓል።
የኢራን ባለስልጣንን ጠቅሶ ሬውተርስ እንደዘገበው በአደጋው የፕሬዝዳንቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሆሴን አሚራብዶላሂያን “ህይወት አደጋ ላይ ነው” ተብሏል።
“አሁንም ድረስ ተስፋ ቢኖረንም አደጋው ከደረሰበት አካባቢ የምንሰማቸው ነገሮች አሳሳቢ ናቸው” ብለዋል ሬውተርስ ስማቸውን ያልጠቀሳቸው ባለስልጣን።
ለአደጋው መንስኤ ነው የተባለው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ የነፍስ አድን ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው የኢራን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አህመድ ቫሂዲ መናገራቸውን የኢራን ዜና አገልግሎት ኢርና ዘግቧል።
የኢራን ጦር ጠቅላይ አዛዥ የሀገሪቱ አብዮታዊ ዘብን ጨምሮ የትኛውም ሀብት ሄሊኮፕተሯ የተከሰከሰችበትን ስፍራ ለመፈለግና ለነፍስ አድን ስራ እንዲውል አዘዋል።
ከ40 በላይ የነፍስ አድን ቡድን አደጋው ደርሶበታል ወደተባለው አርስፓራን ጫካ ቢያመሩም በጉም የተሸፈነው ተራራ ውስጥ የተከሰከሰችውን ሄሊኮፕተር እስካሁን አላገኟትም።
አንዳንድ የኢራን መገናኛ ብዙሃን ፕሬዝዳንት ራይሲ እና ሌሎች አብረዋቸው ሲጓዙ የነበሩ የኢራን ባለስልጣናት አደጋው ከደረሰበት ስፍራ ወጥተው በእግራቸው እየተጓዙ መሆኑን ቢዘግቡም ከቴህራን ባለስልጣናት ማረጋገጫ አልተሰጠም።
የኢራን ብሄራዊ ቴሌቪዥን መደበኛ ስርጭቱን አቋርጦ ሙሉ ትኩረቱን አደጋው ላይ ያደረገ ሲሆን፥ ኢራናውያን ፕሬዝዳንት ራይሲና ልኡካቸው ከአደጋው ይተርፉ ዘንድ እየጸለዩላቸው ነው ተብሏል።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሀሚኒም አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩ ሲሆን፥ በአደጋው ምክንያት የመንግስት ስራ እንደማይስተጓጎል ተናግረዋል።
አያቶላህ ሃሚኒ ለኢራናውያን ያስተላለፉት መልዕክት አደጋው ከባድ ሳይሆን እንደማይቀር አመላካች ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።