ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ በንጹሃን ዜጎች ላይ ባደረሰችው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን ገልጻለች
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መክፈቷን ገለጸች፡፡
ዩክሬን የኔቶ አባል እሆናለሁ ማለቷን ከሩሲያ ጋር ወደለየለት ጦርነት ከገባች ሰባት ወራት ያስቆጠረች ሲሆን ይህ ጦርነት በርካታ ጉዳቶች አስከትሏል፡፡
ሩሲያ ለልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን ምድር ጦሯን ካስገባች በኋላ ዓለማችን በርካታ ክስተቶችን ያስተናገደች ሲሆን የዓለም ምግብና ነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደድ እና ሌሎችም ዋነኛ የዓለማችን ክስተቶች ናቸው፡፡
አራቱ የዩክሬን ግዛቶች ነማለትም ኬርሰን፣ ዛፖራዚየ፣ ሉሃንስክ እና ዶምቴስክ ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ የተቀላቀሉ ሲሆን ዩክሬንም በሩሲያ ቁጥጥር ስር ያሉ ግዛቶቿን ለማስመለስ በጥረት ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ ክሪሚያ ግዛትን ከተቀረወቅ ሩሲያ ጋር የሚያተሳስረው ዋና ድልድይ በዩክሬን መመታቱን ተከትሎ ሩሲያ በዛሬው ዕለት የሚሳዔል ጥቃት ከፍታለች፡፡
የሩሲያ መከላከያ ባወጣው መግለጫ የዩክሬንን ወታደራዊ እና የሀይል መሰረተ ልማት ትኩረት ያደረጉ የሚሳኤል ጥቃቶችን ሰንዝራለች፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ በዩክሬን መዲና ኪየቭን ጨምሮ በርካታ የዩክሬን ከተሞች በሩሲያ ሚሳኤል ጥቃቶችን ያስተናገዱ ሲሆን ዩክሬን በበኩሏ በርካታ ንጹሃን በሩሲያ ሚሳኤል መገደላቸውን አስታውቃለች፡፡
የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች የዓለማችን ሀገራት የሩሲያን የሚሳኤል ጥቃት ያወገዙ ሲሆን ጀርመን ለዩክሬን የአየር ጥቃት መከላከያ መሳሪያ እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
የኔቶ አባል የሆኑ የአውሮፓ ሀገራትም ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲደረግላት በመወትወት ላይ ሲሆኑ ሩሲያ በበኩሏ የዩክሬን መንግስትን በሽብርተኝነት ከሳ እርምጃዋን እንደምትቀጥል ገልጻለች፡፡
አፍሪካን በመጎብኘት ላይ የነበሩት የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሮ ኩሌባ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡