ኢራን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ማባረሯን አስታወቀች
ለስለላ ተሰማርቷል የተባለው ሰው አልባ አውሮፕላኑ የኢራን የአየር ክልልን ሊጥስ ጥቂት ርቀት ይቀረው ነበር ተብሏል

አሜሪካ እስካሁን በኢራን ስለወጣው መግለጫ ያለችው ነገር የለም
ኢራን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ማባረሯን አስታወቀች።
የአሜሪካ ጦር ንብረት ነው የተባለው ሰው አልባ አውሮፕላን በቴህራን አቅራቢያ ቅኝት በማድረግ ላይ ነበር ተብሏል።
የኢራኑ ኤፍ-14 የተሰኘው የውጊያ አውሮፕላን የአሜሪካ ሰው አልባ የስለላ አውሮፕላንን እንዳባረረ ተገልጿል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሁፍ " በየመን ያለው ሁቲ ቡድን ለሚያደርገው እያንዳንዱ ጥቃት ሀላፊነቱን የምትወስደው ኢራን ናት" ብለዋል።
እንዲሁም ሁቲ የሚያደርጋቸው እያንዳንዳቸው ጥቃቶች የጦር መሳሪያ፣ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎችን የምታደርገው ኢራን እንደሆነች ይቆጠራልም ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ።
የኢራኑ ኑር ድረገጽ እንደዘገበው ከሆነ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን በኢራን አየር ክልል አቅራቢያ እያለ በኤፍ-14 የውጊያ አውሮፕላን ከአየር ክልላችን እንዲርቅ ተደርጓል።
የኢራን ጦር ማንኛውንም የውጭ ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆኑን እና በመካከለኛው ምስራቅ የኢራን ጥቅሞችን እንደሚያስከበር አስታውቋል።
እንዲሁም የኢራንን አየር ክልል የሚጥስ ማንኛውንም አካል መትቶ እንደሚጥልም የሀገሪቱ ጦር አስጠንቅቋል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ጦር ማዘዣ እስካሁን የኢራን ጦር ስላወጣው መግለጫ ያለው ነገር የለም።
የአሜሪካ ጦር በየመን ሁቲ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃቶችን በማድረግ ላይ ሲሆን የሁቲ አማጺ ቡድን በምላሹ በቀይ ባህር ባለው የአሜሪካ ባህር ሀይል መርከብ ላይ የባሊስቲክ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ሲሆን አጋርነቱም ለሐማስ እንደሆነ ገልጿል።