ሩሲያ እና ቻይና የኢራን ኒዩክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ የመጠቀም መብት እንዲከበር ጠየቁ
ሶስቱ ሀገራት በቴሄራን የኒዩክሌር ፕሮግራም ዙሪያ በቤጂንግ እየመከሩ ነው

በመድረኩ ላይ ማንኛውም የኒዩክሌር ስምምነት የሁለቱንም ወገን ጥቅሞች ያከበረ ሊሆን እንደሚገባው ጠይቀዋል
አሜሪካ ከቴህራን ጋር አዲስ የኑክሌር ድርድር እንዲደረግ ግፊት እያደረገች በምትገኝበት ወቅት ቻይና እና ሩሲያ ከኢራን ጎን አንደሚቆሙ ገልጸዋል፡፡
ሀገራቱ በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው በኩል በዛሬው ዕለት በቤጂንግ ባደረጉት ውይይት የኑክሌር ድርድር በጋራ መከባበር ላይ እንዲመሰረት እና በቴሄራን ላይ የተጣሉ ሁሉም ማዕቀቦች እንዲነሱ ጠይቀዋል፡፡
በኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ላይ ያተኮረውን ስብሰባቸውን ከጨረሱ በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫ፣ ኢራን የኒዩክሌር መርሃግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ መሆኑን ደጋግማ መግለጿን እንደሚቀበሉት እና ቴህራን በሰላማዊ መንገድ የኒዩክሌር ኃይልን የመጠቀም መብቷ ሙሉ በሙሉ ሊከበርለት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በ2015 ኢራን ከአሜሪካ ፣ ሩሲያ ፣ ቻይና ፣ ብሪታንያ ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ጋር ባደረገችው ስምምነት ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ከተነሱላት የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመግታት ተስማምታለች።
ይህን ስምምነት ለሁለት አመት በስራ ላይ ከቆየ በኋላ ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው በ2018 ቀደው ጥለውታል፡፡
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን እንደሚደግፉት የገለጹት ሩስያ እና ቻይና፤ ነገር ግን በኃይል ከማስፈራራት ፣ ከጫና እና ከማዕቀብ በጸዳ መልኩ በመግባባት ሊከናወን እንደሚገባው አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
የሩሲያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ሪያብኮቭ እና የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ ወደ ቤጂንግ ያቀኑት ኢራን ለትራምፕ እንደራደር ጥያቄ አሉታዊ ምላሽ ከሰጠች ከአንድ ቀን በኋላ ነው፡፡
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ሀሚኒ የትራምፕን የእንደራደር ጥያቄ አስመልከተው ባደረጉት ንግግር" የድርድር ስምምነት ውልን እንደማያከብሩ ስናውቅ መደራደር ምን ዋጋ አለው? ስለዚህ ለመደራደር መጋበዙ ማታለል ካልሆነ ጥቅም የለውም " ሲሉ መናገራቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል፡፡
ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን ለአዲስ የኑክሌር ስምምነት ወደ ጠረጴዛው የማትመለስ ከሆነ ወታደራዊ አማራጭን እንደሚጠቀሙ እየዛቱ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ሳምንት አሜሪካን ጨምሮ 6 የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት ቴሄራንን በተመለከተ በዝግ ያደረጉት ጉባኤም በቤጂንግ ፣ ቴሄራን እና ሞስኮ ተወግዟል፡፡
ሀገራቱ መሰል የተናጠል እርምጃዎች በተደራዳሪ አካላት መካከል አለመተማመንን የሚያሰፋ እና ችግሩ ባለበት እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡