ዮርዳኖስ የኢራንን ድሮኖች እና ሚሳኤሎች መትቶ በመጣል ትልቅ ተሳትፎ ማድረጓ ይታወሳል
የኢራን እና እስራኤል ወቅታዊ ውጥረት ለዮርዳኖስም ተርፏል።
አማን ባለፈው ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ኢራን ወደ እስራኤል የተኮሰቻቸውን ከ300 በላይ ድሮኖችና ሚሳኤሎች በማክሸፉ ሂደት ትልቅ ድርሻ ነበራት።
የኢራን ሚሳኤሎች የዮርዳኖስን የአየር ክልል አቋርጠው የሚያልፉ በመሆናቸውና ሉአላዊነቷን ለማስከበር እርምጃውን መውሰዷን ገልጻለች።
“የህዝባችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ጥቃት ለመመከት እንሰራለን” ያሉት የሀገሪቱ ንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ፥ እርምጃው እስራኤልን ከጥቃት ለመጠበቅ የተፈጸመ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ኢራን ግን በሶሪያ ለተፈጸመባት ጥቃት አጻፋ ነው ያለችውን ጥቃት በመመከት የተሳተፈችውን ዮርዳኖስ “ቀጣዩዋ ኢላማ” ትሆናለች ስትል ማስጠንቀቋን ፋርስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢራን የሚገኙትን የሀገሪቱን አምባሳደር የጠራ ሲሆን፥ ቴህራን የምታቀርበውን “አቋማችሁ ምንድነው” ጥያቄ እንድታቆም ጠይቋል።
እስራኤል ወደ ኢራን ጥቃት ልትሰነዝረው በምትችለው ጥቃት የዮርዳኖስ የአየር ክልል እንዳይጣስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የሀገሪቱ ጦር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
የሀገሪቱ ንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት “ዮርዳኖስ የእስራኤልና ኢራን ጦርነት የቲያትር ሜዳ አትሆንም” ማለታቸውን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
ከጠቅላላ ህዝቧ ግማሽ የሚጠጋው ትውልደ ፍልስጤማውያን የሆኑባት ዮርዳኖስ፥ የፍልስጤም ነጻ ሀገርነትን ከሚደግፉት ትመደባለች።
ከጎረቤቷ እስራኤል ጋርም ከ30 አመት በፊት የሰላም ስምምነት ተፈራርማለች፤ ምንም እንኳን ግንኙነቷን “ቀዝቃዛ ሰላም” ብትለውም። ዮርዳኖስ ከአሜሪካ ጋርም ወዳጅነት መስርታለች።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የዮርዳኖሱ ንጉስ በእስራኤል ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞን እያሰሙ ለፍልስጤማውያን በአውሮፕላኖች ድጋፍ እንዲደርስ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ውጥረት በበዛበት ቀጠና የምትገኘው ሀገር የሰሞኑ የእስራኤልና ኢራን ግጭት አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል።