በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የአስረኛ ልውውጥ ያደራደረችው ኦማን እንደሆነች ተዘግቧል
ኢራን እና ስዊድን ባደረጉት የእስረኛ ልውውጥ በጦር ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ የተባለው ኢራናዊ ተለቋል።
ቴህራን እና ስቶክሆልም ያደረጉት ልውውጥ አውሮፓዊው ዲፕሎማት፣ ሌላ አንድ ሰው እና በ1988 ኢራን ውስጥ በተፈጸመው ግድያ ተባብሯል የተባለው ሀሚድ ኑሪ እንዲለቀቅ አስችሏል።
ኑሪ በ2019 ለጉብኝት በመጣ ወቅት ነበር የተያዘው።ይህን ተከትሎ ኢራን ለረጅም ጊዜ መደራደሪያ አደርጋቸዋለሁ በሚል ሁለት የስዊድን ዜግነት ያላቸውን ሰዎች ማሰሯ ገልጿል።
የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዤን ኑሪ በህገ ወጥ መንገድ መታሰሩን የገለጸ ሲሆን የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ደግሞ ዲፕሎማት ጆሀን ፎሎደሩስ እና የስዊድን ዜግነት ያለው ሰአድ አዚህ "የምድር ሲኦል" ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል።
"ኢራን ሀሚድ ኑሪን ለማስለቀቅ በማሰብ እነዚህን ሁለት ስዊድናውያን መደራደሪያ አድርጋቸዋለች" ሲሉ ክሪስተርሰን በዛሬው እለት ተናግረዋል።
"ይህ ኦፐሬሽን ወይም እስረኛ መቀያየር ከባድ ውሳኔ የሚፈልግ መሆኑ ገልጽ ነው፤ አሁን መንግስት እነዚህን ወሳኔዎች ወስኗል።"
የኢራን መንግስት ሚዲያዎች ኑሪ በኢራን ውስጥ መህራባድ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ አውሮፕላን ሲወጣ እና ከቤተሰቦቹ ጋር ሲተቃቀፍ አሳይተዋል። "ሀሚድ ኑሪ ነኝ። ኢራን ገብቻለሁ" ሲል ተደምጧል።"ፈጣሪ ነጻ አውጥቶኛል" ብሏል ኑሪ።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የአስረኛ ልውውጥ ያደራደረችው ኦማን እንደሆነች ተዘግቧል።
በፈረንጆች 2022 በስቶኮሆልም የሚገኘው ፍርድ ቤት በኑሪ ላይ የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶበት ነበር።