የትራምፕ አስተዳደር ለእስራኤል የ7.4 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭን አጸደቀ
የጦር መሳሪያ ሽያጩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችና ቦምቦችን እንደሚያካትት ተገልጿል
ዴሞክራቶች ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ሽያጭ በኮንግረንሱ መገምገምና መጽደቅ ነበረበት በሚል ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው
አሜሪካ ለእስራኤል 7 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ ተስማማች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጦር መሳሪያ ሽያጩን ማጽደቁን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
6 ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን የሚያቀርበው ቦይንግ ኩባንያ ነው ተብሏል።
የጦር መሳሪያ አምራቹ ሎክሄድ ማርቲን ደግሞ 660 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ "ሄልፊር" ሚሳኤሎችን ያቀባል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኮንግረንሱ ሳያሳውቁና ሳያጸድቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችና ቦምቦችን ሽያጭ ማጽደቃቸው ዴሞክራቶች ትችት እንዲያነሱባቸው አድርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮም የኮንግረንሱን መደበኛ የምርመራ ሂደት ለመተላለፍ የሚያስችል አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም ነው ያሉት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ዴሞክራቶችን የወከሉት ግሪጎሪ ሚክስ።
ተወካዩ "እስራኤል ለተደቀነባት ቀጠናዊ የደህንነት ስጋት ምላሽ እንድትሰጥ ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ እንዳለብን አምናለሁ፤ ነገር ግን የረጅም አመታት ልምዳችን እየተጣሰ መሄዱ ያሳስበኛል" ብለዋል።
ይሁን እንጂ በዴሞክራቱ ጆ ባይደን የስልጣን ዘመንም የኮንግረንሱ ይሁንታ ሳይጠበቅ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጸድቆላታል።
የባይደን አስተዳደር ባለፈው አመት 50 ኤፍ -15 ጄቶችን ጨምሮ 20 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማጽደቁን ሲኤንኤን አስታውሷል።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው በቴል አቪቭ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም ያዛወሩት ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ከተመለሱ በኋላም ለእስራኤል ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ከሰሞኑ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በዋሽንግተን ሲመክሩ ጋዛን ለመቆጣጠር ማቀዳቸውን መግለጻቸውም ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ነቀፌታ አስተናግዶባችዋል።
በጋዛ ከ47 ሺህ በላይ ላለቁበትና ከ230 ሺህ በላይ ቤቶች ለወደሙበት የእስራኤል ድብደባ የአሜሪካ ቦምቦችና ሚሳኤሎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። የትራምፕ አስተዳደር አዲስ የጦር መሳሪያ ሽያጭም የጋዛውን ጦርነት ዳግም አስነስቶ የቴህራን እና ቴል አቪቭ ፍጥጫንም እንዳያንረው ተሰግቷል።