የኢራን ተመራማሪዎች በወራት ውስጥ የኒዩክሌር ቦምብ ለመስራት መጠመዳቸው ተነገረ
የአሜሪካ የደህንነት ምንጮች ኢራን ከአሜሪካ አልያም ከእስራኤል ሊቃጣባት ለሚችል ጥቃት አጻፋውን ለመመለስ እየተዘጋጀች ነው ብለዋል
ቴህራን ግን አውዳሚ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎችን መስራት እንደማትፈልግ በተደጋጋሚ ገልጻለች
የኢራን ተመራማሪዎች በወራት ውስጥ የኒዩክሌር ቦምብ ለመስራት መጠመዳቸው ተነገረ።
ኒውዮርክ ታይምስ የአሜሪካ የደህንነት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ተቀማጭነቱን ቴህራን ያደረገ የተመራማሪዎች ቡድን በአጭር ጊዜ አቶሚክ ቦምብ መስራት የሚያስችል አዲስ አሰራር እያፈላለጉ ነው።
የደህንነት ምንጮቹ ስለአቋራጩ መንገድ "ፈጣን" ነው ከማለት ውጭ ዝርዝር ማብራሪያን አልሰጡም።
የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ኢራን በጥቂቱ አራት አቶሚክ ቦምቦችን መስራት የሚያስችል የኒዩክሌር ነዳጅ እንዳላት ነው የጠቆመው።
በሶሪያ የበሽር አል አሳድ አገዛዝ መወገድ እና ድጋፍ የምታደርግለት የሊባኖሱ ሄዝቦላህ አቅም መዳከም ቴህራን የኒዩክሌር አቅሟን ይበልጥ እንድታጠናክር ማድረጉንም አብራርቷል።
በአሜሪካ የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኢራን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ባለቤት ለመሆን የመቃረብ ጉዳይ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይመክሩበታል ተብሏል።
ኔታንያሁ የቴህራንን የኒዩክሌር ጣቢያዎች ለማውደም በተደጋጋሚ ቢዝቱም በዋሽንግተን ምክር ሳይፈጽሙት መቅረታቸው የሚታወስ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደነጩ ቤተመንግስት ከገቡ በኋላ ከኢራን ጋር ውጥረት ማባባስ እንደማይፈልጉ አሳይተዋል።
ባለፈው ወር እስራኤል በኢራን የኒዩክሌር ጣቢያ ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ድጋፍ ይሰጣሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ ውጥረቱ በዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንዲረግብ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ምዕራባውያን ኢራን በሚስጢር የምታካሂደው የዩራኒየም ማበልጸግ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን ያለመ ስለመሆኑ ይገልጻሉ። ቴህራን ግን ኒዩክሌርን ለሰላማዊ አገልግሎት እንደምትጠቀም በመጥቀስ ክሱን በተደጋጋሚ ውድቅ ታደርጋለች።
ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው (2018) ሀገራቸውን ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት ማስወጣታቸው ይታወሳል። ይህም ቴህራን የተነሱላት ማዕቀቦች ዳግም እንዲጣሉ አድርጎ የዩራኒየም ማበልጸቅ እንቅስቃሴዋ እንዲጨምር ማድረጉ ይነገራል።
አሜሪካን ዳግም ወደ ስምምነቱ ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች የተጋተቱ ቢሆንም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ቴህራን ከምዕራባውያን ጋር "ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግና በመከባበር ላይ የተመሰረተ" ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ ናት ብለዋል።
ከ2024ቱ ምርጫ በፊት ኢራን የግድያ ሙከራ አድርጋብኛለች ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከለዘብተኛው የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ጋር በመምከር የዋሽንግተን እና ቴህራንን ፍጥጫ ያረግቡታል ወይ የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው።