ሳኡዲ አረቢያ ትራምፕ እና ኢራንን አዲስ የኒውክሌር ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማደራደር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች
የቀጠናው አጋሮች መዳከማቸውን ተከትሎ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ምርቷን ልታፋጥን እንደምትችል ተሰግቷል

ንጉሳዊ አስተዳደሩ ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳለው ይነገራል
ሳኡዲ አረብያ አሜሪካ እና ኢራን አዲስ የኒውክሌር ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማሸማገል እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡
ሪያድ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ያላትን የጠበቀ ወዳጅነትን በመጠቀም በቴሄራን እና በአሜሪካ መካከል የዲፕሎማሲ ድልድይ ለመሆን አስባለች፡፡
ሲኤንኤን ባወጣው ዘገባ ሳኡዲ ድርድሩን ለመምራት ይፋዊ ጥያቄ ስለማቀረቧ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ከቀድሞ ባላንጣዋ (ኢራን) ጋር ያላትን የተሻሻለ ግንኙነት ለማጠናከር እና በድርድር ጠረጴዛው ላይ ሚና ለማግኝት ያላትን ፍላጎት አመላካች ነው ብሏል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ሄዝቦላህ፣ ሀማስ እና የበሽር አላሳድ መንግስትን ጨምሮ ሌሎችም ቀጠናዊ አጋሮቿ የተዳከሙባት ቴሄራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ምርቷን ማፋጠን ላይ ልትሰራ እንደምትችል ስጋት ተፈጥሯል፡፡
ይህ ስጋት ከሚመለከታቸው ሀገራት መካከል አንዱ የሆነው ንጉሳዊ አስተዳደሩ የኢራን የኒውክሌር መሳሪያ መታጠቀን ለማስቀረት ከአሜሪካ ጋር አዲስ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማግባባት ቀዳሚ አማራጩ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሳኡዲ አረብያ የ2015ቱን የኒውክሌር ስምምነት እንደምትደግፍ በጊዜው አሳውቃ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ኢራን በሊባኖስ፣ በኢራቅ እና በየመን ከሚገኙ ታጣቂዎች ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለብሔራዊ ደሕንነት ስጋት ነው በሚል የኦባማ አስተዳደር ስምምነቱን እንዲከልስ ጠይቃለች፡፡
በ2018 ትራምፕ ከስምምነቱ መውጣታቸውን በይፋ ሲያስታወቁ ድጋፏን በይፋ መግለጿ ይታወሳል፡፡
ከአመታት በኋላ በሳኡዲ እና በኢራን መካከል የነበረው ውጥረት ቀዝቀዝ ብሎ በ2023 በቻይና አደራደሪነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ድጋሚ ለማስቀጠል ተስማምተዋል፡፡
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ እንደሆኑ ቢናገሩም ከተሄራን ባለስልጣናት በኩል የሚመጣው ምላሽ ግን የተደበላለቀ መሆኑን ሲኤንኤን በዘገባው ጠቅሷል፡፡
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ሀሚኒ ከአሜሪካ ጋር መደራደር ብልህነት አይደለም ሲሉ፤ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ዋሽንግተን ሁለቱንም ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ ስምምነት የምታቀርብ ከሆነ ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሳኡዲ ባለስልጣናት የአሁኑን ቀጠናዊ ገጽታ ከኢራን ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ እና ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እንደ ታሪካዊ አጋጣሚ አድርገው ይመለከቱታል፡፡
ከዚህ ባለፈም አሜሪካ ወይም እስራኤል ከኢራን ጋር በሚያደርጉት ማንኛውም አይነት ግጭት ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደማይፈልጉ አጥብቀው ይገልጻሉ።