አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ለፈጸመችው ጥቃት በጋራ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ አስታወቁ
ኢራን ጥቃት የሚከፈትባት ከሆነ በሁሉም የእስራኤል መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ዝታለች
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ሀይል እንደሚሰማራ ተናግረዋል
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ለፈጸመችው ጥቃት በጋራ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ አስታወቁ
ትላንት ምሽት ከ200 በላይ የባላስቲክ ሚሳይሎች የዘነቡባት እስራኤል ምንም እንኳን ስጠብቀው የነበረ ጥቃት ቢሆንም ኢራን በብዙ እጥፍ ተባዝቶ የሚመለስ ትልቅ ስህተት ሰርታለች ስትል ዝታለች፡፡
ሚሳይሎቹን በማክሸፍ ከቴልአቪቭ ጋር ያበረችው አሜሪካ በበኩሏ ከእስራኤል ጋር በመወገን በኢራን ላይ የጋር አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
ከወትሮው ከፍ ባለ ውጥረት ውስጥ በሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ኢራን ትላንት ምሽት ያስወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች ቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ስጋት አባብሰውታል፡፡
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መረጃ በምሽቱ ጥቃት በቴልአቪቭ እና በዙርያው የሚገኙ ሶስት ወታደራዊ ካምፖችን ኢላማ አድርጊያለሁ ብሏል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎም እስራኤል ባወጣችው መግለጫ አብዛኛዎቹ ሚሳይሎች መክሸፋቸውን ስትገልጽ በቀጣይ ከኢራን ባለፈ በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ላይም የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች፡፡
ሀገሪቱ ጥቃት አደርስባቸዋለሁ ያለቻቸው የቀጠናውን ሀገራት በስም ባትገልጽም ኢራን የምትደግፋቸው ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል የሚባሉት ኢራቅ ፣ የመን እና ሶርያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኢራን በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል ለዚህ በሰጠችው ምላሽ የምሽቱ ጥቃት ለሀማሱ የፖለቲካ ቢሮ መሪ እስማኤል ሀኒየህ እና ለሄዝቦላው መሪ ሀሰን ናስረላህ ግድያ የሰጠነው የአጸፋ ምላሽ ተጠናቋል፤ ነገር ግን ተጨማሪ ጥቃት የሚደርስብን ከሆነ በእስራኤል ሁሉም መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንፈጽማለን ብላለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይድን በበኩላቸው ከእስራሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በቀጣይ እርምጃዎች ዙሪያ በመምከር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ሚንስትራቸው ሎይድ ኦስተን ደግሞ በቀጠናው አሜሪካ ተጨማሪ ሀይል እንደምታሰማራ አስታውቀዋል፡፡
በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ አጋሮችን እና ጥቅሟን ለማስከበር ዋሽንግትን ሀያሏን ማስጠጋቷን ያስታወቁት ሚንስትሩ በቀጣይ ተጨማሪ ሀይል በሚሰማራባቸው ስፍራዎች ዙርያ ከእስራኤል መከላከያ ሀይል ጋር በመነጋጋገር ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ ስፍራው ማቅናታቸወን ነው ያስታወቁት፡፡
ከጋዛው ጦርነት በኋላ የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰበት የመጣው መካከለኛው ምስራቅ ሁሉን አቀፍ ቀጠናዊ ግጭት ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚሉ ስጋቶች በርትተውበታል፡፡
ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በሊባኖስ የምታደርሰውን ጥቃት አጠናክራ የቀጠለችው እስራኤል በደቡባዊ የሀገሪቱ ድንበር አቅራቢያ የምድር ላይ ዘመቻውችን እያደረገች ትገኛለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀጠናው ወደ ማይወጣበት የተባባሰ ጦርነት ውስጥ ከመገባቱ በፊት በግጭቱ ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት ውጥረትን ከማባባስ እንዲቆጠቡ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በመወትወት ላይ ነው፡፡