ኢራን በትራምፕ ላይ ግድያ ለመፈጸም አላሴርኩም አለች
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን በተመራጩ ፕሬዝዳንት እና በአሜሪካ መንግስት ሲቀርቡ የነበሩ ወቀሳዎችን ውድቅ አድርገዋል
ትራምፕ ከተቃጣባቸው ሁለት የግድያ ሙከራዎች ጋር በተያያዘ የቴህራን እጅ ስለመኖሩ አልተረጋገጠም
ኢራን ሪፐብሊካኑን ዶናልድ ትራምፕ ለመግደል ሞክራለች በሚል የቀረበባትን ወቀሳ ውድቅ አደረገች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ከአሜሪካው ኤንቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "(ትራምፕን) ለመግደል አልሞከርንም ፤ ወደፊትም አናደርገውም" ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው በህዳር ወር 2024 ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ትዕዛዝ ተቀብሎ ትራምፕን ለመግደል ሲንቀሳቀስ ነበር ያለውን ኢራናዊ በቁጥጥር ስር አውሏል።
ትራምፕም በ2024ቱ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ጀርባ ኢራን ልትኖር እንደምትችል በተደጋጋሚ መናገራቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
የፊታችን ሰኞ ወደ ዋይትሃውስ የሚዘልቁት ትራምፕ በፍሎሪዳ ዌስት ፓልም ቢች ጎልፍ ሲጫወቱ እና በፔንሲልቫኒያ በልተር ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሁለት የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል።
ይሁን እንጂ መርማሪዎች ኢራን በእነዚህ ሁለት የግድያ ሙከራዎች ላይ ተሳትፎ እንዳላት የሚያሳይ መረጃን አላገኙም።
ቴህራን ከግድያ ሙከራው ባሻገር በሳይበር ጥቃት በዋሽንግተን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እየሞከረች ነው በሚል የሚቀርብባትን ተደጋጋሚ ክስም ፕሬዝዳንት ፔዝሽኪያን አጣጥለውታል።
ለዘብተኛ አቋም አላቸው የሚባልላቸው ፔዝሽኪያን የኢራን የኒዩክሌር ፕሮግራም ሰላማዊ መሆኑንና ቴህራን የኒዩክሌር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን እየሰራች እንደማትገኝ ተናግረዋል።
አሜሪካን ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት ያስወጡት ትራምፕ ዳግም መመረጥን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም "ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በመላው አለም ሰላም እንዲሰፍን ይሰራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ጦርነት አንፈራም፤ ግን አንፈልገውም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከትራምፕ ጋር በኒዩክሌር ዙሪያ ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን በመጥቀስም "ችግሩ ከንግግሩ ሳይሆን ከድርድር በኋላ ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች መፈጸሙ ላይ ነው" ብለዋል።
ኢራን እና የአውሮፓ ሀገራት (ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን) በቴህራን የኒዩክሌር ፕሮግራም ዙሪያ ከሰኞ ጀምሮ ንግግር ጀምረዋል።
ምክክሩ አሜሪካ በ2018 ከኒዩክሌር ስምምነቱ ከወጣች በኋላ በኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ እና ቴህራንም የዩራኒየም ክምችቷን በመጨመር የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንድትገታ የሚያስችል ድርድር እንዲጀመር በር ይከፍታል ተብሏል።