አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ልዑክ በኢራን ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
ጡረተኛው ጀነራል በኢራን ድክመቶች ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል
የኢራን ተቃዋሚ ፓርቲ በፈረንሳይ ፓሪስ ዓለም አቀፍ አጋርነት መድረክ አካሂደዋል
አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ልዑክ በኢራን ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን በድርድር ለማስቆም በሚል ጡረተኛው የቀድሞው የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጁነራል ኬት ኬሎግን መሾማቸው ይታወሳል።
እኝህ የሰላም ልዑክ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በተካሄደ አንድ የኢራን ተቃዋሚ መድረክ ላይ " በቴህራን ላይ የመጨረሻው ጫና እንዲደረግ ተናግረዋል።
በኢራኑ ብሔራዊ መከላከል ምክር ቤት የተዘጋጀው ይህ ዓለም አቀፍ መድረክ የአውሮፓ እና አሜሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተገኝተዋል።
የዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን ልዑክ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ኢራን ላይ የመጨረሻውን ጫና ማድረስ አለብን ብለዋል።
"ኢራንን በዘላቂነት ለማሻሻል በኢራን ድክመት ላይ ማተኮር አለብን፣ ለዚህም መዘግየት የለብንም" ሲሉም ጀነራል ኬት ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ "ፈረንሳይ የሽብር ቡድኖች በሀገሯ ማስተናገዷን ተችቷል።
ፈረንሳይ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ያወጣችውን ዓለም አቀፍ ህግ እንደጣሰችም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
የኢራን ዋና አጋር የነበረው የሶሪያው የቀድሞ መንግሥት ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ወደ ሞስኮ ከኮበለሉ በኋላ መፍረሱ ይታወሳል።
እንዲሁም የሊባኖሱ ሂዝቦላህ በእስራኤል ጦር በደረሰበት ጥቃት እንደተዳከመ ይገለጻል።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ከረር ያለ አቋም እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን መንግስታቸው ተጨማሪ ጫና ሊያደርሱ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ኢራን በበኩሏ ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፒዮ እና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቷ ይታወሳል።