“እስራኤል ሀገር አይደለችም፤ የወንጀለኞችና ሽብርተኞች መከማቻ እንጂ” - ሃሚኒ
የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ መሱድ ፔዝሽኪያን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ይሁንታ ሰጥተዋል
ፕሬዝዳንት ፔዝሽኪያን የፊታችን ማክሰኞች ቃለመሃላ ይፈጽማሉ
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ መሱድ ፔዝሽኪያን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በይፋ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
በድጋሚ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ለዘብተኛው ፔዝሽኪያን ከሃሚኒ ድጋፍ ማግኘታቸውን ተከትሎ የፊታችን ማክሰኞ ቃለመሃላ ይፈጽማሉ ተብሏል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት በጋዛ የቀጠለው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት በቀጠለበትና እስራኤል በሊባኖስ ጦርነት ለመጀመር ጫፍ ላይ በደረስበት ወቅት ነው ሃላፊነት የሚመጡት።
እስራኤል ከወደ ሊባኖስ በሄዝቦላህ የተተኮስ ሮኬት በጎላን ኮረብታ በእግርኳስ ሜዳ ላይ አርፎ በጥቂቱ 12 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን አስታውቃ በሊባኖስ የቡድኑ ይዞታዎች ላይ ድብደባ ጀምራለች።
በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎችን ትደግፋለች የምትባለው ቴህራን እስራኤል በሊባኖስ ጦርነት ከጀመረች ከባድ ዋጋ እንደምትከፍል በዛሬው እለት ባወጣቸው መግለጫ አሳስባለች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ይሁንታ ሲሰጡ ባደረጉት ንግግርም የሀገራቸውን የረጅም ጊዜ “ጸረ እስራኤል” አቋም አንጸባርቀዋል።
“የጺዮናዊው መንግስት (እስራኤል) ሀገር አይደለችም፤ የወንጀለኞች፣ ወሮበላ ቡድን፣ የገዳዮችና ሽብርተኞች መከማቻ እንጂ” ያሉት ሃሚኒ፥ በአንጻሩ በጋዛ አይበገሬነቱን እያሳየ ነው ያሉትን ሃማስ አወድሰዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንትም ምንም እንኳን ለዘብተኛ ናቸው ቢባልም ከሁለት ቀናት በኋላ ቃለመሃላ ፈጽመው ስልጣን ሲይዙ ይህንኑ የሃማኒ ሃሳብ ማስተጋባታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ቴህራን ከምዕራባውያን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ እሰራለሁ በሚል ቃል የገቡት ፔዝሽኪያን፥ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም ይጠበቃል።
በቀጣይ የካቢኔ አባላትን ሲመርጡም በተለይ የውጭ ጉዳይ፣ የደህንነት እና የነዳጅ ሚኒስትሮች ሹመት የመጨረሻው ውሳኔ በ85 አመቱ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ላይ የተመሰረተ ይሆናል ነው የተባለው።
በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ኢብራሂም ራይሲ የተኩት ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ከቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች በበለጠ በማዕቀብ የተጎዳውን የቴህራን ኢኮኖሚ ለማንሰራራትና የስራ እድል ለመፍጠር ከባድ የቤት ስራ አለባቸው።