የኢራን ጦር “ጠላት የጦር ጄቶች የአየር ክልላችንን ጥሰው እንዳይገቡ መከላከል ችለናል” ብሏል
ኢራን “ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የፈጸመችው ጥቃት ያስከተለው ዝቅተኛ ጉዳት ነው ያደረሰው” በማለት የእስራኤልን ጥቃት አጣጥላለች።
እስራኤል በዚህ ወር መጀመርያ አካባቢ ከኢራን ለተፈጸመባት የሚሳኤል ጥቃት የአጸፋ እርምጃ ነው ያለችውን ጥቃት ትናንት ማለዳ ላይ በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ፈጽማለች።
በርካታ የእስራኤል ጄቶች በቴህራን አቅራቢያ እና በምዕራብ ኢራን አቅራቢያ በሚገኙ በሚሳኤል ፋብሪካዎች እና በሌሎች ቦታዎች ላይ በሶስት ዙር የተከፈለ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ የእስራኤልን የአየር ድብደባ በማውገዝ፤ ኢራን ራሷን የመከላከል ምብት እና ግዴታ አለባት ብሏል።
የኢራን ጦር በበኩሉ፤ እስራኤል በኢላም እና ኩዜስታን ግዛቶች ድንብር አቅራቢያ ላይ የሚገኙ የኢራን ራዳር ስርዓት ላይ ቀለል ያሉ ሚሳዔሎችን ተጠቅመው ጥቃት መሰንዘራቸወን አስታውቋል።
የአየር መከላከያ ስርዓቷ ከእስራኤል የተሰነዘረውን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ መከላከል ችሏል ያለው ጦሩ፤ በቴህራን፣ ኩዜስታን እና ኢላም ግዛቶች በሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ይፋ አድርጓል።
“ጠላት የጦር ጄቶች የአየር ክልላችንን ጥሰው እንዳይገቡ መከላከል ችለናል” ያለው የኢራን ጦር፤ የደረሰው ጉዳትም በጣም አነስተኛ ነው በማለት የእስራአቴልን ጥቃት አጣጥሏል።
እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ ስትወተውት የነበረችው አሜሪካ፤ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው የግጭት አዙሪት እንዲቆም ጥሪ አቅርባለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት የእስራኤል ጥቃት የኢራን ወታደራዊ ተቋማት ኢላማ ያደረገ ነው፤ ይህ "መጨረሻው" እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።
የእስራል ጦር በትናት ማለዳው ጥቃት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ጥቅም ላይ ስለማዋሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የእስራኤል ጥቃት በቴሄራን፣ ኩዜስታን እና ኢላም ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ለአራት ሰአታት የፈጀው ጥቃት 6 ከተሞችን እና 20 ኢላማዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተሰምቷል።