ኪየቭና አጋሮቿ ኢራን ድሮኖችን ጨምሮ ለሩሲያ ትጥቅ አቅርባለች በሚል በተደጋጋሚ ከሰዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በሩሲያ ወዳጅ ኢራን ላይ ለ50 ዓመታት የሚዘልቅ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ረቂቅ ህግ አቅርበዋል።
የዘለንስኪ ጽ/ቤት ኃላፊ አንድሪይ ያርማክ ማዕቀቡ ቴህራን ለሞስኮ "ለምታቀርበውን የጦር መሳሪያ" ምላሽ ነው ብለዋል።
ኪየቭ እና አጋሮቿ ባለፈው ዓመት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ለሩሲያ ትጥቅ ሰጥታለች በሚል በተደጋጋሚ ከሰዋል።
ቴህራን ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
ረቂቅ ህጉ በዩክሬን ፓርላማ ከጸደቀ፤ የኢራን እቃዎች በዩክሬን መጓጓዝ እና የአየር ክልሏን መጠቀምን ከማስቆም በተጨማሪ በኢራን እና በዜጎቿ ላይ የንግድ፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ማዕቀቦችን እንደሚጣሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
ኪየቭ እንዳስታወቀችው ሞስኮ እሁድ እለት በአንድ ጀንበር ትልቁን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ጥቃት ፈጽማለች።
ለዚህም 54 "ኢራን ሰራሽ" ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተጠቅማለች። 52 ያህሉ በጥይት ተመትተዋል ተብሏል።