የሳኡዲ ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቻይና ተገናኙ
ሚኒስትሮቹ በቤጂንግ የተገናኙት የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሪያድ ጉብኝት እንደሚያደርጉ በተገለጸ ማግስት ነው
በቻይና ንአደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሀገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን በሁለት ወራት ውስጥ ይከፍታሉ
የሳኡዲ አረቢያ እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ በቤጂንግ ተገናኝተዋል።
ልኡል ፈይሰል ቢን ፈርሃን የኢራን አቻቸውን ሁሴን አሚርአብዱላሂያን ሲጨብጡ እና ለውይይት ሲቀመጡ የሚያሳይ ምስልን የሳኡዲ ብሄራዊ ቴሌቪዥን በትዊተር ገጹ ላይ ለጥፏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በቻይና ሸምጋይነት የተደረሰው እርቅን ወደ ተግባር መለወጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች እንደሚወያዩ ተገልጿል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሪያድ ጉብኝት እንዲያደርጉ የቀረበላቸውን ግብዣ በተቀበሉ ማግስት እየተካሄደ ያለው ውይይት ሻክሮ የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማደስ ትልቅ ድርሻ አለው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ሳኡዲ መቼ እንደሚገቡ ግን እስካሁን አልተገለጸም ብሏል ዘናሽናል በዘገባው።
የመካከለኛው ምስራቅ ጂኦፖለቲካን ለመቆጣጠር የሚፎካከሩት ሳኡዲ እና ኢራን በፈረንጆቹ 2016 ሳኡዲ ታዋቂ የሺያ እስልምና አባትን ከገደለች በኋላ መሻከሩ የሚታወስ ነው።
በቴህራን የሚገኘው የሳኡዲ ኤምባሲ በተቃዋሚዎች ከተደበደበ በኋላም ሀገራቱ ከየመን እስከ ሶሪያ በእጅ አዙር ሲፋለሙ መቆየታቸው አይዘነጋም።
ከአንድ ወር በፊት በቤጂንግ አደራዳነት የተደረሰው ስምምነት ግን የሰባት አመቱን ሰጣገባ አብርዶ ወደ ሰላማዊ ንግግር መልሷቸዋል።
የረመዳን ጾም ሲጀመር በስልክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነጋገሩት የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ዛሬ በቤጂንግ በአካል ተገናኝተው ውይይት ጀምረዋል።
በስምምነቱ መሰረት ሀገራቱ የተዘጉ ኤምባሲዎቻቸውን በሁለት ወራት ውስጥ ይከፍታሉ።
ሳኡዲ እና ኢራን ከሚያዚያ 2021 ጀምሮ ለአምስት ያህል ጊዜ በኢራቅ መዲና ባግዳድ ድርድሮችን ማድረጋቸውም ተገልጿል።