ኢራን በእስራኤል ላይ አዲስ ጥቃት ከከፈተች “ከባድ ዋጋ ትከፍላለች” ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች
እስራኤልም ኢራን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን ወታደራዊ አቅሟን የሚያዳክም ማዕቀብ እንዲጣልባት ጠይቃለች
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በእስራኤልና ኢራን ወቅታዊ ፍጥጫ ዙሪያ መክሯል
ኢራን በእስራኤል ላይ አዲስ ጥቃት ከከፈተች “ከባድ ዋጋ ትከፍላለች” ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በኢራን እና እስራኤል ወቅታዊ ፍጥጫ ዙሪያ ሲመክር ነው ዋሽንግተን ማስጠንቀቂያውን ያሰማችው።
ኢራን በእስራኤልና በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከፈጸመች “ያለምንም ማመንታት ራሳችን ለመከላከል እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ።
ባለፈው ቅዳሜ እስራኤል በኢራን ላይ የወሰደችው የአጻፋ እርምጃ የመጨረሻው የተኩስ ልውውጥ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ያሉት አምባሳደሯ፥ አሜሪካ ውጥረቱ እንዲባባስ እንደማትፈልግ ተናግረዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር አሚር ሳይድ ኢራቫኒ ዋሽንግተን ለቴል አቪቭ “ህገወጥ እና ኢሞራላዊ ወታደራዊ ድጋፍ” እያደረገች ቴህራንን የወሰደችውን ራስን የመከላከል እርምጃ ማውገዝ አትችልም ሲሉ ተቃውመዋል።
ኢራን ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን በመጥቀስም “በሉአላዊነታችን ላይ ለሚቃጣ ጥቃት ግን አጻፋውን የመመለስ መብት አለን” ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል በበኩሏ 15 አባል ሀገራት ባሉት የጸጥታው ምክርቤት፥ ኢራን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን ወታደራዊ አቅሟን የሚያዳክም ማዕቀብ እንዲጣልባት ጠይቃለች።
በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ባለፈው ቅዳሜ በኢራን ላይ የተፈጸመው ጥቃት “ተመጣጣኝ” መሆኑን ተናግረዋል።
“እስራኤል ጦርነት አትፈልግም፤ (ኢራን) ጸብ አጫሪ ድርጊቷን ከገፋችበት ግን ፈጣንና ከባድ እርምጃ መውሰዳችን አይቀርም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
በጸጥታው ምክርቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ያላት ቻይና በበኩሏ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስና የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት የማስቆሙ ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቃለች።
በተመድ የቻይና አምባሳደር ፉ ቾንግ አሜሪካን በስም ባትጠቅሱም በጸጥታው ምክርቤት የቀረቡ የጋዛ ተኩስ አቁም እቅዶችን ውድቅ ያደረገችውን ዋሽንግተን “መጀመሪያ የንጹሃንን ሞት ማትረፍ እና ጦርነት ማስቆም ይቅደም” ሲሉ ተችተዋል።
የሩሲያው አምባሳደር ቫስሊ ኔቤንዚያም አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ የወቅታዊው ውጥረት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ነው ያብራሩት።
“እስራኤል ከጎረቤቶቿ ጋር የገባችበትን ግጭት ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ሃይል እንዲሆን ያደረገው ከዋሽንግተን የሚደረግላት ድጋፍና ከለላ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ሌላኛዋ የእስራኤል አጋር ብሪታንያ በበኩሏ ኢራን ለባለፈው ሳምንቱ የእስራኤል ጥቃት ምላሽ እንዳትሰጥ አሳስባለች።
ቴህራን ግን ለቴል አቪቭ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጀች መሆኑ እየተዘገበ ነው።