በሶስት ዙር ተደርጓል የተባለው ጥቃት በዋናነት አራት የኢራን ወታደራዊ ተቋማት ላይ ኢላማ ያደረገ ነው
“የእስራኤል ጦር ተልዕኮውን አጠናቀቀ፤ አውሮፕላኖቻችንም በሰላም ተመለሱ” እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የጀመረችውን ጥቃት ማብቃቱን የገለጸችበት ሀሳብ ነበር፡፡
ቅዳሜ ማለዳ ከቴሄራን በስተ ምዕራብ በርካታ ፍንዳታዎች ሲሰሙ የኢራን ባለስልጣናት ፍንዳታዎቹ እስራኤል የተኮሰቻቸውን ሚሳኤሎች ለማክሸፍ የተሰማሩ የአየር መቃወሚዎች ያሰሙት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የእስራኤል ጥቃት በቴሄራን፣ ኩዜስታን እና ኢላም ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ለአራት ሰአታት የፈጀው ጥቃት 6 ከተሞችን እና 20 ኢላማዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ቅዳሜ ንጋት ላይ በእስራኤል ጥቃት መፈጸሙን ባስታወቀበት መግለጫ የእስራኤል ጦር የኢራን አገዛዝ እና በአካባቢው ያሉ አጋሮቹ ከጥቅምት 7 2023 ጀምሮ በሰባት ግንባሮች እስራኤልን ማጥቃት አላቆሙም ብሏል፡፡
ጦሩ ለተቃጣበት ጥቃት ምላሽ የመስጠት መብትም ግዴታም አለበት ያለው መግለጫ የመከላከያ ሀይሉ በማጥቃት እና በመከላከል ላይ ነው ሲል አስታውቋል፡፡
በ6 ከተሞች በሶስት ደረጃዎች የተፈጸመው የእስራኤል ጥቃት በዋናነት አራት አይነት ወታደራዊ ተቋማትን ያካተተ ነበር፡፡
ከነዚህ ተቋማት መካከል ባለፈው አንድ አመት በእስራኤል ላይ ከሄዝቦላህ ፣ ከሁቲ ታጣቂዎች እና ከራሷ ኢራን ጥቃት ለመፈጸም የዋሉ ሚሳኤሎች የሚመረቱበት ፋብሪካ አንድኛው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ዲዛይን ማድረጊያ እና ማበልጸጊያ ፣ የጦር መሳርያ ማምረቻ ፣ የባላስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያ ስፍራዎች እና የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂ የተገጠመባቸው ቦታዎች የጥቃቱ ኢላማዎች ነበሩ፡፡
በተመሳሳይ ሌሎች ወታደራዊ ካምፖች እና ማዘዣዎችም በጥቃቱ የተካተቱ ሲሆን ቴሄራን፣ አህቫዝ፣ ሺራዝ ፣ አባዳን፣ ካራጅ እና ከርማንሻህ ከተሞች ላይ በአየር እና በሚሳኤል ጥቃት ማድረሱ ነው የተገለጸው፡፡
ሲኤንኤን በምንጭነት የጠቀሳቸው የኢራን ባለስልጣናት እስካሁን ጥቃቶቹ ያደረሱትን ትክክለኛ የጉዳት መጠን ለመናገር ሁኔታዎች ግልፅ አይደሉም ሲሉ፤ የእስራኤል ጦር በበኩሉ በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ትክክለኛ እና ኢላማን መሰረት ያደረገ የአየር ድብደባና የባለስቲክ ሚሳኤል ትቃት አድርጌያለሁ ብሏል።