በኢራን በተፈጸመ ጥቃት 10 የጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ
ከቴህራን 1 ሺህ 200 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኝ ከተማ ለተፈጸመው ጥቃት እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም
እስራኤል በኢራን በፈጸመችው የአጻፋ እርምጃ ሁለት ወታደሮች መገደላቸውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስታውቋል
በደቡብ ምስራቅ ኢራን በተፈጸመ ጥቃት 10 የጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ።
በኮንቮይ ሲጓዙ የነበሩት ፖሊሶች ከቴህራን በ1 ሺህ 200 ኪሎሜትር ርቅ በምትገኘው ጎላር ኩህ ከተማ ነው መገደላቸው የተገለጸው።
ታስኒም እና መኸርን ጨምሮ የኢራን መገናኛ ብዙሃን በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት እንጂ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን አላወጡም።
የኢራን ብሄራዊ ዜና አገልግሎት ኢርናም በፖሊስ ኮንቮይ ላይ “በህገወጦች” ጥቃት ደርሷል ከማለት ውጪ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም።
የከተማዋ ፖሊስ ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ ጥርጣሬውን አልገለጸም፤ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካልም የለም።
10 ፖሊሶች የተገደሉበት ጥቃት እስራኤል ለጥቅምት መጀመሪያው የኢራን የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ምላሽ በሰጠች በስአታት ውስጥ ነው የተፈጸመው።
እስራኤል በኢራን ምዕራባዊ እና ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት የሁለት ወታደሮችን ህይወት መቅጠፉ ተዘግቧል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወታደራዊ ተቋማት ላይ አነጣጥሮ ለተፈጸመው የእስራኤል ጥቃት ቴህራን አጻፋውን የመመለስ መብት አላት ብሏል።
እስራኤል በበኩሏ ቴህራን ሌላ ዙር ጥቃት ከፈጸመች ከባድ ዋጋ ትከፍላለች ስትል ዝታለች።
10 ፖሊሶች ከተገደሉበት ጥቃት ከእስራኤል ጋር ስለመገናኘቱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።