እስራኤል ጥቃት ከመፈጸሟ በፊት ኢራን ምላሽ እንዳትሰጥ የሚያስጠነቅቅ መልእክት ልካ እንደነበር ተገለጸ
እስራኤል ይህን መልእክት የላከችው በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለውን የጥቃት ልውውጥ ለመገደብ እና ግጭቱ ቀጣናዊ መልክ እንዳይዝ ለማድረግ ነው ተብሏል
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን እና ኢራን ወደ ቀጥተኛ ግጭት እንዳያስገባቸው ተሰግቷል
እስራኤል ጥቃት ከመፈጸሟ በፊት ኢራን ምላሽ እንዳትሰጥ የሚያስጠነቅቅ መልእክት ልካ እንደነበር ተገለጸ።
እስራኤል በኢራን ላይ የበቀል እርምጃ ከመውሰዷ በፊት ባለፈው አርብ እለት ምላሽ እንዳትሰጥ የሚያስጠነቅቅ መልእክት ልካ እንደነበር አክሲዮስ የተባለው የዜና ድረ ገጽ ሶሰት ለጉዳዩ ቅርብ ናቸው ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ እስራኤል ይህን መልእክት የላከችው በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለውን የጥቃት ልውውጥ ለመገደብ እና ግጭቱ ቀጣናዊ መልክ እንዳይዝ ለማድረግ ነው።
የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለስልጣናት እስራኤል በዛሬው እለት ጧት በኢራን ላይ በሶስት ዙር ጥቃት ፈጽማለች ብለዋል። የመጀመሪያው ዙር በኢራን የአየር መከላከያ ስርአት ላይ ያተኮረ ሲሆን ሁለተኛው እና ሶስተኛው ዙሮች ደግሞ በሚሳይል እና በድሮን ጣቢያዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ኢራን የእስራኤል ጥቃት ማክሸፏን እና በወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የደረሰው ጉዳት የተወሰነ እንደሆነ ገልጻለች። የእስራኤል ባለስልጣናት ጥቃቱን የፈጸሙት ኢራን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በ200 ገደማ ሚሳይሎች ያደረሰችባትን ጥቃት ለመበቀል ነው።
አክሲዮስ እንደዘገበው ከሆነ የእስራኤል መልእክት የደረሰው በበርካታ ሶስተኛ ወገኞች ነው።
"እስራኤል ምን ልታጠቃ እንደምትችል ቀደም ብላ ለኢራን ማሳወቋን" አክሲየስ ያናገረው አንደኛው ምንጭ ተናግሯል። ሌሎች ሁለቱ ምንጮች ደግሞ ኢራን ለጥቃቱ ምላሽ እንዳትሰጥ ማስጠንቀቋን እና ኢራን ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ እና በተለይ ንጹሃን ከተጎዱ ወይም ከተገደሉ እስራኤል ከባድ ምላሽ እንደምትሰጥ አስምራ መናገሯን ገልጸዋል።
ኢራን ከእስራኤል ጋር ወደ አጠቃላይ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ፣ ነገርግን ከተጠቃች ምላሽ እንደመትሰጥ ስትገልጽ ቆይታለች
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ኢራን ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ በመስጠት ውጥረት የምታባብስ ከሆነ እስራኤል የበቀል እርምጃ ለመውረድ ትገደዳለች ብለዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣን እንደገለጹት አሜሪካ በእስራኤል ዘመቻ አትሳተፉም፣ ነገርገን ኢራን የበቀል እርምጃ የምትወስድ ከሆነ አሜሪካ እስራኤልን ከእንዲህ አይነት ጥቃት ለመጠበቅ ዝግጁ ነች።
አክሲዮስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ከእስራኤል ጥቃት በፊት የኢራን መልእክት ያደረሱት የኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካስፓር ቬልድካምፕ ናቸው።
"ሰለጦርነቱ እና በቀጠናው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለደረሰው ውጥረት ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተነጋግሬያለሁ። ሁሉም አካላት ግጭት ከማባባስ እንዲታቀቡ አሳስባለሁ" ሲሉ ቬልድካምፕ እስራኤል ጥቃት ከመፈጸሟ ከሰአታት በፊት በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን እና ኢራን ወደ ቀጥተኛ ግጭት እንዳያስገባቸው ተሰግቷል።