ኢራን በእስራኤል ጥቃት የሚሳይል ምርቷ አለመስተጓጎሉን ገለጸች
የእስራኤል የመከላከያ ሚንስትር ባለፈው ሳምንት በተፈጸመው የአየር ጥቃት የኢራን የሚሳይል ማምረቻዎች ተጎድተዋል ብለው ነበር
ቴሄራን “ጠላታችን የመከላከል እና የማጥቃት ስርዓቶቻችንን ለመጉዳት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም” ብላለች
የሚሳይል ምርቷን ለማስተጓጎል የተፈጸመው ጥቃት በምርት ሂደቱ ላይ የታሰበውን ጉዳት አለማድረሱን ኢራን አስታወቀች፡፡
የኢራን የመከላከያ ሚንስትር አዚዝ ናስርዛዴህ በጥቃቱ የተስተጓጎለ ስራ አለመኖሩን እና የሚሳኤል ምርት ሂደቱ መቀጠሉን ለመንግስት ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እስራኤል ከኢራን ለተፈጸመባት ጥቃት በሶስት ዙር የተመራ የአጸፋ ምላሽ መስጠቷን ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡
በ6 ከተሞች በ20 ኢላማዎች ላይ ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት በዋናነት አራት ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡
ከነዚህ ተቋማት መካከል ባለፈው አንድ አመት በእስራኤል ላይ ከሄዝቦላህ ፣ ከሁቲ ታጣቂዎች እና ከራሷ ኢራን ጥቃት ለመፈጸም የዋሉ ሚሳይሎች የሚመረቱበት ፋብሪካ አንድኛው ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ዲዛይን ማድረጊያ እና ማበልጸጊያ ፣ የጦር መሳርያ ማምረቻ ፣ የባላስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፊያ ስፍራዎች እና የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂ የተገጠመባቸው ቦታዎች የጥቃቱ ኢላማዎች ነበሩ፡፡
ሰኞ እለት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የእስራኤል አብራሪዎች “የኢራንን የሚሳይል የማምረት አቅም ላይ ጉዳት በማድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሚንስትሩ በንግግራቸው በጥቃቱ የኢራን የመከላከል እና የማጥቃት አቅም ላይ ኪሳራ አድርሰናል ብለዋል፡፡
ሮይተርስ የአሜሪካ ወታደራዊ ተንታኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው የእስራኤል የአየር ድብደባ ኢራን ለባለስቲክ ሚሳኤሎች ጠንካራ ውህዶችን ለመደባለቅ የምትጠቀምባቸውን ህንጻዎች በመምታቱ በሀገሪቱ ሚሳይሎችን በጅምላ የማምረት አቅም ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ጠቅሷል፡፡
የኢራን የመከላከያ ሚንስትር አዚዝ ናስርዛዴህ በበኩላቸው “ጠላታችን ሁለቱንም የመከላከል እና የማጥቃት ስርዓቶቻችንን ለመጉዳት ፈልጎ ነበር፤ ነገርግን ብዙም አልተሳካለትም ምክንያቱም ቀድመን ስለምናውቅ በቂ ዝግጅት አድርገን ነበር” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የሚሳይል ምርት እውቀቱ ሀገር በቀል በመሆኑ በሚሳኤል ማምረቻ ሂደት ላይ ምንም አይነት መስተጓጎል አለመግጠሙን ፣ ጉዳት የደረሰባቸው የአየር መከላከያ መሳሪያዎችም በማግስቱ በአዲስ መተካታቸውን ገልጸዋል፡፡
መከላከያ ሚንስትሩ ተሄራን አሁንም የጥቅምት አንድ አይነቱን ጥቃት በእስራኤል ላይ የመፈጸም ሙሉ አቅም አላት ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ከሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስረላህ ግድያ በኋላ ኢራን180 የሚጠጉ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን ተከትሎ እስራኤል ልትወስድ የምትችለው የበቀል እርምጃ በስጋት ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡
ከጥቃቱ ቀደም ብሎ ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው ቴሄራን በእስራኤል ላይ ድጋሚ የአጸፋ እርምጃ ለመውስድ እየመከረች እንደምትገኝ የተለያዩ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡