ዓለም ትኩረቱን በአሜሪካ ምርጫ ላይ ባደረገበት ወቅት ሩሲያ ከዩክሬን ሁለት መንደሮች መቆጣጠሯ ተገለጸ
የሩሲያ ጦር በዶኔትስክ ክልል የሚገኙ ሁለት መንደሮችን ከዩክሬን ጦር ቀምቻለሁ ብሏል
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ዶናልድ ትራምፕን እንኳን ደስ አለዎት ማለታቸው ይታወሳል
ዓለም ትኩረቱን በአሜሪካ ምርጫ ላይ ባደረገበት ወቅት ሩሲያ ከዩክሬን ሁለት መንደሮች መቆጣጠሯ ተገለጸ።
በአሜሪካ ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ዋነኛ አጀንዳ የነበረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ይህን ጦርነት እንደሚያስቆሙት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ዓለም ሁሉ በዚህ ምርጫ ላይ ትኩረቱን ባደረገበት ወቅት የሩሲያ ጦር ከዩክሬን ሁለት መንደሮችን እንደተቆጣጠረ አስታውቋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በዶኔትስክ ክልል የሚገኙት አንቶኒቭካ እና ማክሲምቪካ የተሰኙ መንደሮችን ተቆጣጥረናል ማለቱን አናዶሉ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የሩሲያ ደቡባዊ እና ምስራቃዊ ጦር አባላት ሁለቱን መንደሮች ተቆጣጥሯል።
እንደ።ሚንስቴሩ መግለጫ ከሆነ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሩሲያ ጦር 648 አውሮፕላን፣ 283 ሂልኮፕተር፣ ከ35 ሺህ በላይ ድሮን፣ 585 የአየር መቃወሚያ እና ሌሎች የውጊያ መሳሪያዎችን አውድሟል ብሏል።
ይሁንና ዩክሬን እስካሁን በሩሲያ ጦር ተይዘዋል ስለተባሉት መንደሮች እና ሌሎች ጉዳቶች ዙሪያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነትን አስቆማለሁ ላሉት ዶናልድ ትራምፕ በእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸው አብረው ለመስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው የዩክሬን ጦርነትን በሰላም ለመቋጨት ዝግጁ መሆናቸውን ለዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸው ላይ አክለዋል።