ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን እንደያዙ ሊያደርጓቸው የሚችሉት ውሳኔዎች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ለአንድ ቀን ብቻ አምባገነን መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል
ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን ጥር 6 በይፋ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ስራ ይጀምራሉ
ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን እንደያዙ ሊያደርጓቸው የሚችሉት ውሳኔዎች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
ዶናልድ ትራምፕ እና ካማላ ሀሪስ ላለፉት ወራት ሰፊ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የቆዩትበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ትናንት ተጠናቋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን አሸንፈዋል።
ካማላ ሀሪስ ሽንፈታቸውን በጸጋ መቀበላቸውን ያሳወቁ ሲሆን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን በሚቆዩባቸው አራት ዓመታት ምን ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚለው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ትራምፕ ከዚህ በፊት ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ወቅት ስልጣን በያዙበት ዕለት አምባገነን መሪ መሆን እፈልጋለሁ ከዛ በኋላ ግን በፍጹም አምባገነን አልሆንም ሲሉ ተናግረው ነበር።
ቢቢሲ የአሜሪካ ፖለቲካ ተንታኞችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ አምባገነን በሚሆኑበት ዕለት ሊያደርጓቸው የሚችሉ ሰባት ክስተቶችን ዘርዝሯል።
በዚህም መሰረት ዶናልድ ትራምፕ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ውጤት ለማስቀየር ሞክረዋል በሚል በርካታ ክስ እንዲመሰረትባቸው ምክንያት የሆኑት ጃክ ስሚዝን ከስራ እንደሚያባርሩ ይጠበቃል ተብሏል።
ሁለተኛው ጉዳይ ትራምፕ ምርጫውን ተጭበርብረዋል በሚል ከጥር ስድስት ነውጥ ጋር በተያያዘ ለእስር ለተዳረጉ ደጋፊዎቻቸው ምህረት እንደሚያደርጉላቸውም ይጠበቃል።
ሌላኛው ዶናልድ ትራምፕ ሊያደርጉት ይችላል የተባለው ጉዳይ ሰነድ አልባ እና ህገወጥ ስደተኞችን ወደመጡበት ሀገር እንዲባረሩ ውሳኔዎችን ሊያሳልፉ ይችላሉም ተብሏል።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል በገቡት መሰረት የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት እንዲቆም ለዩክሬን ድጋፍ ማድረግን ማቆም እና የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ጫና ማድረግ እንደሚጀምሩም ይጠበቃል።
ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ግብር እንዲከፍሉ፣ የኑሮ ውድነቱን መቀነስ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተብሎ የተወሰኑ ውሳኔዎችን መሻር እና ሌሎች ተያያዥ ውሳኔዎችን ሊወስኑ ይችላሉም ተብሏል።
እንዲሁም አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ አጥር ለመገንባት የጀመሩት ጥረት እንዲተፈጸም ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደሚችሉም ተገልጿል።